YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ዕዝራ 1

1
አይሁድ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ቂሮስ መፍቀዱ
1እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ አማካይነት አስቀድሞ የተናገረውን የትንቢት ቃል የፋርስ ተወላጅ ቂሮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ፈጸመው፤ ይኸውም እግዚአብሔር ራሱ ቂሮስን አነሣሥቶ ከዚህ የሚከተለውን ትእዛዝ በጽሑፍ በማወጅ በንጉሠ ነገሥት ግዛቱ ሁሉ እንዲነበብ አደረገ። #ኤር. 25፥11።
2የፋርስ ንጉሠ ነገሥትም በዐዋጅ የሰጠው ትእዛዝ እንዲህ የሚል ነበር፦ “የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የዓለም ሁሉ ገዢ አድርጎኛል፤ እርሱም ቤተ መቅደስን በይሁዳ ምድር በምትገኘው በኢየሩሳሌም እንድሠራለት አዞኛል። #ኢሳ. 44፥28። 3ከእናንተ መካከል የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆነ ሁሉ፥ አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በይሁዳ ወደሚገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣና የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይሥራ። 4እነዚህ ከሞት የተረፉት ሰዎች በሚመለሱበት ጊዜ በአካባቢአቸው የሚኖሩ ሰዎች ብርና ወርቅ፥ ዕቃና የጭነት ከብቶች ይርዱአቸው፤ ይህም በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ቤተ መቅደስ በፈቃዳቸው ከሚሰጡት መባ ሌላ ነው።”
5ከዚያም በኋላ የይሁዳና የብንያም ነገዶች የቤተሰብ አለቆች፥ ካህናትና ሌዋውያን፥ እንዲሁም እግዚአብሔር ልቡን ያነሣሣው ሌላውም ሰው ሁሉ፥ ተመልሶ ለመሄድና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንደገና ለመሥራት ተዘጋጀ። 6ጐረቤቶቻቸውም ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎችን፥ ቈሳቊሶችንና ከብቶችን፥ ሌሎችንም ጠቃሚ የሆኑ ስጦታዎችና በቤተ መቅደስ መባ ሆኖ የሚቀርብ ሌላም ነገር በመለገሥ ረዱአቸው።
7ከዚህም በቀር ቂሮስ ቀድሞ ንጉሥ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ዘርፎ በመውሰድ በአማልክቱ ቤተ መቅደስ ያኖራቸውን እንደ ጽዋ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት መልሶ ሰጣቸው። 8የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ እነዚያን ንዋያተ ቅድሳት ሚትረዳት ተብሎ በሚጠራው በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ግምጃ ቤት ኀላፊ አስቈጥሮ የይሁዳ ገዢ ለሆነው ለሼሽባጻር አስረከበው፤ 9-10የዕቃውም ዝርዝር እንደሚከተለው ነበር፦
ለመባ መሰብሰቢያ የሚሆኑ ከወርቅ የተሠሩ ሳሕኖች 30
ለመባ መሰብሰቢያ የሚሆኑ ከብር የተሠሩ ሳሕኖች 1000
ሌሎች ልዩ ልዩ ሳሕኖች 29
ከወርቅ የተሠሩ ወጭቶች 30
ከብር የተሠሩ ወጭቶች 410
ሌሎች ልዩ ልዩ ዕቃዎች 1000
11ሼሽባጻር ከሌሎቹ ስደተኞች ጋር ሆኖ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሰ ጊዜ ያመጣቸው ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎች ድምር 5400 ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in