YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ሕዝቅኤል 46

46
የእስራኤል መሪና የበዓላቱ አከባበር
1ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገባው ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ የሚያመለክተው በር በስድስቱ የሥራ ቀኖች ዝግ መሆን አለበት፤ ነገር ግን በሰንበት ቀንና በየወሩ መባቻ ቀን ይከፈታል። 2መስፍኑ በመግቢያው ክፍል በኩል ከውጪ አደባባይ ወደ ውስጥ ገብቶ በቅጽሩ በር መቃን አጠገብ ይቆማል፤ ካህናቱ ደግሞ እርሱ ያዘጋጀውን የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ መስፍኑም በመድረኩ ላይ እንዳለ ይሰግዳል፤ ከዚያ በኋላ እርሱ ይወጣል፤ የቅጽሩ በር ግን እስከ ምሽት ድረስ አይዘጋም። 3በእያንዳንዱም ሰንበትና በየወሩም መባቻ ሕዝቡ ሁሉ በምሥራቁ መግቢያ በር በኩል ለእግዚአብሔር ይስገዱ።
4“መስፍኑ በሰንበት ቀን በሙሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ምንም ነውር የሌለባቸውን ስድስት የበግ ጠቦቶችና አንድ የበግ አውራ ለእግዚአብሔር ያቅርብ። 5ከእያንዳንዱም የበግ አውራ ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ እህል ያምጣ፤ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ጠቦት ጋር ለማቅረብ የፈለገውን ያኽል ያቅርብ፤ ከእያንዳንዱም ኢፍ መሥዋዕት ጋር አብሮ የሚቀርብ ሦስት ሊትር ዘይት ያምጣ። 6በእያንዳንዱ የወር መባቻ ደግሞ ምንም ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈን፥ ስድስት የበግ ጠቦቶችና አንድ የበግ አውራ ያቅርብ። 7ከእያንዳንዱ ኰርማና ከእያንዳንዱ የበግ አውራ ጋር አንድ አንድ ኢፍ የእህል መባ ይሁን፤ እንዲሁም ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋር የሚቀርበው መባ መስፍኑ ለመስጠት የፈቀደውን ያኽል ይሁን፤ ከእያንዳንዱም ኢፍ ጋር ሦስት ሊትር የወይራ ዘይት አብሮ ይቅረብ። 8መስፍኑም ሲገባ በበሩ መተላለፊያ በኩል ገብቶ ሲወጣም በዚያው በኩል ይውጣ።
9“በማናቸውም የበዓል ቀን ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ለመስገድ በሚመጡበት ጊዜ በሰሜን ቅጽር በር የገቡት በደቡብ ቅጽር በር ይውጡ፤ በደቡብ ቅጽር በር የገቡትም በሰሜን ቅጽር በር ይውጡ፤ ማንም ሰው በገባበት በር አይውጣ፤ ነገር ግን በአንጻሩ ባለው በሌላ በር መውጣት አለበት። 10መስፍኑም ሕዝቡ በሚገቡበት ጊዜ ገብቶ፥ በሚወጡበት ጊዜ ይውጣ። 11በታላላቅና በታናናሽ በዓላት ቀኖች ከእያንዳንዱ ኰርማና ከእያንዳንዱ የበግ አውራ ጋር የሚቀርበው የኽህል መባ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ይሁን፤ ለእግዚአብሔር የሚሰግደው ሰው ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋር የፈቀደውን ያኽል ያቅርብ። ከእያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ መባ ጋር ሦስት ሊትር የወይራ ዘይት አብሮ ይቅረብ።
12“በሥልጣን ላይ ያለው መስፍን በሙሉ የሚቃጠልም ሆነ ወይም የደኅንነት መሥዋዕት በበጎ ፈቃደኛነት በግሉ ለእግዚአብሔር ማቅረብ ቢፈልግ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገባው የምሥራቁ በር ይከፈትለት፤ የመባውንም አቀራረብ በሰንበት ቀን በሚያደርገው ዐይነት ይፈጽም፤ እርሱም ወጥቶ ከሄደ በኋላ በሩ ይዘጋ።”
በየዕለቱ የሚቀርብ መሥዋዕት
13እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “መስፍኑ በየማለዳው የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት የበግ ጠቦት ማዘጋጀት አለበት። 14ከእርሱም ጋር በየማለዳው ሳያስታጒል ሁለት ኪሎ ያኽል የእህል ቊርባንና ለምርጡ ዱቄት መለወሻ እንዲሆን አንድ ሊትር ዘይት ያዘጋጃል። ይህም የዘወትር ሥርዓት ይሆናል። 15በዚህም ዓይነት የበጉ ጠቦት፥ የእህሉ ቊርባንና ዘይቱ በየማለዳው መቅረብ ያለበት የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።”
መስፍኑና የምድሪቱ ይዞታ
16ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በሥልጣን ላይ ያለው መስፍን ከርስቱ ላይ ቀንሶ ከልጆቹ ለአንዱ ቢሰጥ ያ ርስት ለርሱና ለራሱ ቤተሰብ ጸንቶ ይቈያል። 17ነገር ግን በሥልጣን ላይ ያለው መስፍኑ የራሱ ድርሻ ከሆነው ርስት ከፍሎ ከአገልጋዮቹ ለአንዱ ቢሰጥ፥ በኀምሳ ዓመት ዞሮ በሚመጣው በኢዮቤልዩ ዓመት ለመስፍኑ ይመለስለት፤ ንብረቱ የራሱ ስለ ሆነ ይዞታው ለዘለዓለሙ የእርሱና የልጆቹ ብቻ መሆን አለበት። #ዘሌ. 25፥10። 18በሥልጣን ላይ ያለው መስፍን ርስት ከሕዝቡ ነጥቆ መውሰድ የለበትም፤ ለልጆቹ ከፍሎ የሚሰጠው መሬት ለራሱ ከተመደበለት ድርሻ ላይ ብቻ መሆን አለበት፤ በዚህም ዐይነት የርስት ድርሻቸውን በመቀማት ሕዝቤን አይጨቊን።”
መሥዋዕት የሚዘጋጁበት ልዩ ክፍል
19ከዚያ በኋላ ያ ሰው በበሩ ጥግ መግቢያ በኩል በሰሜን ወዳለው የተቀደሱ የካህናት መደዳ ክፍሎች ወደ ሆኑት አመጣኝ፤ ከክፍሎቹም በስተ ምዕራብ መጨረሻ አንድ ቦታ አየሁ። 20እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ ቦታ ካህናቱ ለኃጢአትና ለበደል ማስተስረያ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን ሥጋ የሚቀቅሉበትና የእህል መሥዋዕት የሚጋግሩበት ክፍል ነው፤ በዚህም ዐይነት በሕዝቡ ላይ ጒዳት እንዳይደርስ ከተቀደሰው መሥዋዕት ሁሉ ወደ ውጪው አደባባይ አይወጣም።”
21ከዚያም በኋላ ያ ሰው ወደ ውጪው አደባባይ አምጥቶ በአራቱ ማእዘን አዞረኝ፤ በያንዳንዱም ማእዘን አንድ አደባባይ ነበር። 22በአራቱ ማእዘኖች ያሉት ትናንሽ አደባባዮች እኩል ነበሩ፤ እያንዳንዳቸውም አርባ ክንድ ርዝመትና ሠላሳ ክንድ ወርድ ነበራቸው። 23በእነዚህም አራት አደባባዮች ዙሪያ በውስጥ በኩል አጭር ግንብ ነበራቸው፤ በግንቦቹም ሥር የእሳት ማንደጃዎች ነበሩ። 24ያም ሰው “እነዚህ ሁሉ የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች፥ ሕዝቡ የሚያቀርበውን መሥዋዕት የሚያበስሉባቸው ክፍሎች ናቸው” አለኝ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in