ትንቢተ ሕዝቅኤል 43
43
የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጠው ደማቅ ብርሃን ወደ ቤተ መቅደስ መመለሱ
1ያ ሰው በምሥራቅ አቅጣጫ ወደሚገኘው የቅጽር በር ወሰደኝ፤ 2እዚያም የእስራኤል አምላክ ክብር ከወደ ምሥራቅ እየተገለጠ ነበር፤ ድምፁም እንደ ኀይለኛ የውሃ ማዕበል ነበር፤ የክብሩ ነጸብራቅም በምድር ላይ አበራ። #ሕዝ. 10፥3-4፤ 18፥19፤ 11፥22-23፤ ራዕ. 1፥15። 3ይህም ራእይ ከዚህ በፊት እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት በመጣ ጊዜ ያየሁትን ይመስል ነበር፤ በኬባር ወንዝ አጠገብ ካየሁትም ራእይ ጋር ይመሳሰላል፤ በዚያን ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ። 4የእግዚአብሔር ክብር በምሥራቁ የቅጽር በር በኩል አልፎ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ።
5የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ላይ አነሣኝ፤ ወስዶም ወደ ውስጠኛው አደባባይ አስገባኝ፤ ቤተ መቅደሱም በእግዚአብሔር ክብር ተሞልቶ ነበር፤ 6በዚያም ያ ሰው በአጠገቤ ቆሞ ነበር፤ እግዚአብሔርም ከቤተ መቅደሱ እንዲህ እያለ ሲናገረኝ ሰማሁ፤ 7እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ይህ በእስራኤላውያን መካከል ለዘለዓለም በምኖርበት ዙፋኔና የእግሬ ማሳረፊያ ነው፤ እስራኤላውያንና ንጉሦቻቸው ከእንግዲህ ወዲህ ጣዖት በማምለክና በንጉሦቻቸው ሞት ጊዜ በሚያደርጉአቸው ድርጊቶች ስሜን አያሰድቡም። 8ነገሥታቱ የቤተ መንግሥታቸውን መድረኮችና መቃኖች ወደ ቤተ መቅደሴ መድረኮችና መቃኖች አስጠግተው ስለ ሠሩ፥ የእኔን ቤትና የእነርሱን ቤት የሚለይ አንድ ግንብ ብቻ ሆኖአል፤ በፈጸሙትም አጸያፊ ድርጊት ሁሉ ቅዱስ ስሜን አሰድበዋል፤ ከዚህም የተነሣ በቊጣዬ አጠፋኋቸው። 9ከእንግዲህ ወዲህ ግን ለጣዖቶች መስገዳቸውን ማቆምና የንጉሦቻቸውንም ሬሳ ከዚህ ማስወገድ አለባቸው፤ ይህን ቢያደርጉ እኔ በእነርሱ መካከል ለዘለዓለም እኖራለሁ።”
10ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤል ሕዝብ ስለ ቤተ መቅደሱ አሠራር ንገራቸው፤ ንድፉንም ያጥኑ፤ ኃጢአት የሞላበት ሥራቸውንም በማስታወስ እንዲያፍሩ አድርጋቸው። 11ባደረጉት ነገር ሁሉ የሚያፍሩ ከሆነ ስለ ቤተ መቅደሱ አሠራር ንድፍ፥ ስለ አደረጃጀቱ ስለ መውጫዎቹና ስለ መግቢያዎቹ፥ ስለ አጠቃላይ፥ አሠራሩ ሁኔታ፥ ስለ ሥነ ሥርዓቱ፥ ስለ ሕጎቹ ሁሉ አስረዳቸው፤ አጠቃላይ ንድፉን አጥንተው ሥርዓቱን ሁሉ ተግባራዊ ያደርጉ ዘንድ በእነርሱ ፊት ጻፈው። 12የቤተ መቅደሱም ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ጫፍ ላይ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ያለው ክልል በሙሉ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል።”
የመሠዊያው አሠራር
13የመሠዊያውም ልክ እንደሚከተለው ነው፦ መሠዊያው ያረፈበት አንድ ረጅም ክንድ ርዝመትና አንድ ረጅም ክንድ ወርድ ሲሆን የዙሪያ ጠርዙም ስፋት አንድ ስንዝር ነው፤ ይህም ረጅም ክንድ በሌላው አንድ ክንድ ከጋት ይሆናል፤ ይህም የመሠዊያው ከፍታ ነው። #ዘፀ. 27፥1-2፤ 2ዜ.መ. 4፥1። 14መሬት ላይ ካረፈው መሠረት ተነሥቶ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ከፍታው ሁለት ክንድ፥ ወርዱ አንድ ክንድ ነበር። ከትንሹ እርከን እስከ ትልቁ እርከን ድረስ ከፍታው አራት ክንድ፥ ወርዱ አንድ ክንድ ነበር። 15መሥዋዕቱ የሚቃጠልበት ይህ የላይኛው መጨረሻ እርከን አራት ክንድ ከፍታ ነበረው፤ በአራቱ ማእዘኖች ላይ ያሉት የመሠዊያው ቀንዶች ከመሠዊያው ጫፍ ላይ ካለው ክፈፍ በላይ ከፍ ያሉ ነበሩ። 16እሳቱ የሚነድበት ክፍል አራት ማእዘን ሲሆን የያንዳንዱ ማእዘን ርዝመት ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበር። 17የላይኛው እርከን እንደ ሌሎቹ እኩል አራት ማእዘን ነበረው፤ እነርሱም ዐሥራ አራት ክንድ ርዝመትና ዐሥራ አራት ክንድ ወርድ ሲሆኑ የጠርዙ ዙሪያ ግማሽ ክንድ ስፋት ነበረው፤ የማረፊያውም ዙሪያ አንድ ክንድ ስፋት ነበረው፤ መወጣጫዎቹም በስተምሥራቅ በኩል ነበሩ።
የመሠዊያው መቀደስ
18ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ‘የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለማቅረብና በእርሱ ላይ ደምን ለመርጨት ይህ መሠዊያ በተሠራ ጊዜ በመሠዊያው ላይ የሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት እንደሚከተለው ይሆናል። 19በፊቴ ቆመው እኔን ለሚያገልገሉ የሌዊ ነገድ ከሆነው ከሳዶቅ ዘር ለተወለዱ የኃጢአት ሥርየት መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ዘንድ ለእነርሱ አንድ ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፤’ ይላል ልዑል እግዚአብሔር። 20አንተም ከደሙ ትንሽ ወስደህ በመሠዊያው ጫፍ በአራቱ ማእዘን ያሉትን የመሠዊያውን ቀንዶች በመሠዊያው እርከን ላይ ያሉትን አራት ማእዘኖችና የመሠዊያውን ጠርዝ ሁሉ ትቀባቸዋለህ፤ በዚህም ሁኔታ መሠዊያውን ታነጻውና ትቀድሰዋለህ። 21ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውንም ኰርማ ወስደህ ለቤተ መቅደሱ ከተከለለው የተቀደሰ ቦታ ውጪ ለዚህ በተወሰነው ስፍራ ታቃጥለዋለህ። 22በማግስቱ ምንም ነውር የሌለበትን አንድ አውራ ፍየል ወስደህ የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አድርገህ ታቀርበዋለህ፤ በኰርማውም ደም ባደረግኸው ዐይነት በፍየሉ ደም መሠዊያውን ታነጻለህ። 23ይህንን ሁሉ ከፈጸምክ በኋላ ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ ከመንጋው ወስደህ፥ 24ሁለቱንም ወደ እኔ ወደ እግዚአብሔር ታቀርባቸዋለህ፤ ካህናቱም ጨው ከነሰነሱባቸው በኋላ ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡአቸዋል። 25ሰባት ቀን ሙሉ በእያንዳንዱ ዕለት አንድ ፍየል፥ ከመንጋው አንድ ወይፈንና፥ አንድ የበግ አውራ፥ የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አድርገህ ታቀርባለህ፤ እነዚህም ሁሉ ነውር የሌለባቸው መሆን አለባቸው። 26መሠዊያው የነጻ ይሆን ዘንድ ለሰባት ቀን የሚቀደስበትን ሥርዓት ያካሄዳሉ፤ በዚህም መሠዊያው የተቀደሰ ይሆናል። 27እነዚህ ቀኖች ካለፉ በኋላ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ካህናቱ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕታችሁን ያቀርባሉ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፤” ይላል ልዑል እግዚአብሔር። #ዘፀ. 29፥35-37።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 43: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997