ትንቢተ ሕዝቅኤል 22
22
የኢየሩሳሌም ሕዝብ የፈጸሙት በደል፤
1እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! በነፍሰ ገዳዮች የተሞላችውን ከተማ ልትፈርድባት ተዘጋጅተሃልን? እንግዲያውስ የፈጸመቻቸውን አጸያፊ ነገሮች ሁሉ ገልጠህ አሳያት። 3ለከተማይቱ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፦ በውስጥሽ ያሉትን ብዙዎችን ስለ ገደልሽና ጣዖቶችን በማምለክ ራስሽን ስላረከስሽ እንድትጠፊ የተወሰነበት ጊዜ ተቃርቦአል። 4በፈጸምሽው ግድያ በደለኛ ሆነሻል፤ በሠራሻቸውም ጣዖቶች ረክሰሻል፤ ስለዚህ የምትጠፊበት ጊዜ ቀርቦአል! ያፋጠንሽውም አንቺ ነሽ። ሕዝቦች እንዲቀልዱብሽ፥ አገሮችም በንቀት አመለካከት እንዲያፌዙብሽ ያደረግኹትም ስለዚህ ነው። 5ስምሽ የጠፋ የሁከት ከተማ ሆይ! በቅርብና በሩቅ ያሉ አገሮች በንቀት አመለካከት ያፌዙብሻል። 6በውስጥሽ ያሉ የእስራኤል መሪዎች ሁሉ እንደየ ሥልጣናቸው የግድያ ወንጀል ይፈጽማሉ፤ 7በውስጥሽም አባትና እናት ይናቃሉ፤ የውጪ አገር ሰዎች ይታለላሉ፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶችና አባትና እናት የሌላቸው ልጆች ይበደላሉ። #ዘፀ. 20፥12፤ 22፥21-22፤ ዘዳ. 5፥16፤ 24፥17። 8ለእኔ የተቀደሱ በሆኑ ነገሮች ላይ አክብሮት የላችሁም፤ ሰንበቴንም አረከሳችሁ። #ዘሌ. 19፥30፤ 26፥2። 9ከእናንተ አንዳንዶቹ ሌሎችን ለማስገደል ሐሰት ይናገራሉ፤ አንዳንዶቹ ለጣዖት የተሠዋውን ሁሉ ይመገባሉ፤ አንዳንዶቹ ዘወትር ፍትወታቸውን ለማርካት ይጣደፋሉ። 10አንዳንዶቹ ከእንጀራ እናታቸው ጋር በመተኛት የአባታቸውን አልጋ ይደፍራሉ፤ አንዳንዶቹ በወር አበባ ጊዜ ውስጥ ያሉትን ሴቶች በማስገደድ ግንኙነት ይፈጽማሉ። 11አንዳንዶቹ ከጐረቤቶቻቸው ሚስቶች ጋር ያመነዝራሉ፤ ሌሎችም ምራቶቻቸውን ይደፍራሉ፤ እንዲሁም ከአባት የተወለዱትን እኅቶቻቸውን ያረክሳሉ፤ #ዘሌ. 18፥7-20። 12ከሕዝብሽ አንዳንዶቹ ገንዘብ ተቀብለው ሰው ይገድላሉ፤ አንዳንዶቹ ለገዛ ወገኖቻቸው ለእስራኤላውያን ሳይቀር በአራጣ ያበድራሉ፤ እነርሱንም በመበዝበዝ ያለ አግባብ ይበለጽጋሉ፤ እኔንም ፈጽሞ ረስተዋል፤” ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። #ዘፀ. 22፥25፤ 23፥8፤ ዘሌ. 25፥36-37፤ ዘዳ. 16፥19፤ 23፥19።
13“ዝርፊያችሁንና ነፍስ መግደላችሁን በመቃወም በእናንተ ላይ እጄን አነሣለሁ። 14እኔ እናንተን በምቀጣበት ጊዜ ወኔ የሚቀርላችሁ ይመስላችኋልን? ወይስ ለመከላከል ኀይል የሚኖራችሁ ይመስላችኋልን? እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ፤ የተናገርኩትንም ቃል እፈጽማለሁ። 15ሕዝብሽን ወደየአገሩና ወደየሕዝቡ እበትናለሁ፤ ክፉ ሥራሽም እንዲያከትም አደርጋለሁ፤ 16ሌሎች አሕዛብ ያዋርዱሻል፤ ስለዚህም አንቺ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቂያለሽ።”
17እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 18“የሰው ልጅ ሆይ! እስራኤላውያን ለእኔ ምንም አይጠቅሙኝም፤ እነርሱ ለእኔ ብር በእሳት ከነጠረ በኋላ ዝቃጩ እንደሚቀር የመዳብ፥ የቆርቆሮ፥ የብረትና የእርሳስ ዝቃጭ ናቸው። 19ስለዚህ እነርሱ እንደ ማዕድን ዝቃጭ ስለ ሆኑ ሁሉንም በአንድነት ሰብስቤ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣቸዋለሁ፤ 20ብር፥ መዳብ፥ ብረት፥ እርሳስና ቆርቆሮ ተሰብስበው ወደ ማቅለጫ እንደሚጨመሩና እንዲቀልጡ እሳት ከስር እንደሚነድባቸው እኔም እናንተን በኀይለኛ ቊጣዬ ሰብስቤ እንድትቀልጡ አደርጋለሁ። 21አዎ በኢየሩሳሌም እሰበስባቸዋለሁ፤ እሳትንም አቀጣጥዬ በቊጣዬ አቀልጣቸዋለሁ። 22ብር በምድጃ ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እነርሱም በእርስዋ ውስጥ ይቀልጣሉ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር የቊጣዬን ኀይል እንዳወረድኩባቸው ያውቃሉ።”
የእስራኤል መሪዎች በደል
23እግዚአብሔር እንደገና እንዲህ አለኝ፦ 24“የሰው ልጅ ሆይ! ምድራቸው ስለ ረከሰች በቊጣዬ ዝናብ እንዳይዘንብ በማድረግ ልቀጣት የተዘጋጀሁ መሆኑን ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ 25መሪዎቻቸው፥ በገደሉአቸው እንስሶች ዙሪያ እንደሚያገሡ አንበሶች ናቸው፤ ሕዝቡንም በጭካኔ ይገድላሉ፤ ገንዘብም ሆነ ሌላ ንብረት ያገኙትን ሁሉ ይወስዳሉ፤ በግድያቸውም ብዙዎችን ሴቶች ያለ ባል አስቀርተዋል። #22፥25 መሪዎቻቸው፦ በዕብራይስጥ ነቢያት ይላል። 26ካህናቱ ሕጌን ይጥሳሉ፤ ቅዱስ ለሆነ ነገርም አክብሮት የላቸውም፤ ቅዱሱን ከርኩሱ አይለዩም፤ ንጹሕ በሆነና ባልሆነ ነገር መካከል ያለውን አያስተምሩም፤ ሰንበትንም ያቃልላሉ፤ ከዚህ የተነሣ የእስራኤል ሕዝብ እኔን አያከብሩኝም። #ዘሌ. 10፥10። 27ባለ ሥልጣኖቹ፥ የገደሉትን እንስሳ እንደሚቦጫጭቁ ተኲላዎች ናቸው፤ ያለ አግባብ ለመበልጸግ ሰውን ይገድላሉ፤ 28ነቢያቱ ግድግዳን ኖራ እንደሚቀባ ሰው ይህን ሁሉ ኃጢአት ይሸፍናሉ፤ በሐሰት ራእይ አየን ይላሉ፤ የውሸት ትንቢትም ይናገራሉ፤ ይህ የልዑል እግዚአብሔር ቃል ነው ይላሉ፤ ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር ምንም ቃል አልነገርኳቸውም። 29የሀገሪቱ ሰዎች ዝርፊያና ቅሚያ ያካሄዳሉ፤ ድኾችን፥ ችግረኞችንና መጻተኞችን ፍትሕ በመንሣት ይበድላሉ። 30በቊጣዬ አገሪቱን ከማጥፋቴ በፊት የቅጽር ግንብ የሚሠራ፥ ቅጽሮቹ በፈረሱበት በኩል በመቆም በእኔና በሕዝቡ መካከል ገብቶ ቊጣዬን የሚያበርድ ሰው ፈለግኹ፤ ነገር ግን ማንንም አላገኘሁም። 31ስለዚህ ቊጣዬን በእነርሱ ላይ አወርዳለሁ፤ በኀይለኛ ቊጣዬም አጠፋቸዋለሁ፤ በደላቸውንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ።” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 22: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997