YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘጸአት 40

40
የድንኳኑ መተከልና የአገልግሎት መጀመር
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2“የመጀመሪያው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ትከል። 3ዐሥሩ ትእዛዞች የተጻፉበትን ጽላት የያዘውን የቃል ኪዳኑን ታቦት በውስጡ አኑር፤ ለመከለያ የተሠራውንም መጋረጃ ከፊት ለፊቱ አድርግ። 4ጠረጴዛውንም ወደ ውስጥ አስገብተህ የመገልገያ ዕቃዎችን በእርሱ ላይ አኑር፤ መቅረዙንም አስገብተህ መብራቶቹን በእርሱ ላይ አኑር፤ 5ዕጣን የሚቃጠልበትን የወርቅ መሠዊያ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት አቁመው፤ በድንኳኑም መግቢያ ደጃፍ መጋረጃውን ስቀል። 6የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ በድንኳኑ መግቢያ ፊት አኑር። 7የመታጠቢያውን ሣሕን በድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠህ ውሃ ሙላበት። 8አደባባዩን በዙሪያው ትከል፤ መጋረጃውንም በድንኳኑ መግቢያ ደጃፍ ላይ ስቀለው።
9“ከዚያም በኋላ ድንኳኑን ከመገልገያ ዕቃዎቹ ጋር የቅባቱን ዘይት በመቀባት ለእግዚአብሔር የተለየ አድርገው፤ የተቀደሰም ይሆናል። 10ቀጥሎም መሠዊያውን ከመገልገያ ዕቃዎቹ ጋር በመቀባት ለእግዚአብሔር የተለየ አድርገው፤ ፈጽሞም የተቀደሰ ይሆናል። 11የመታጠቢያውንም ሳሕን ከነማስቀመጫው በዚሁ ዐይነት ቀብተህ ለእግዚአብሔር የተለየ አድርግ።
12“አሮንንና ልጆቹን ወደ ድንኳን ደጃፍ አምጥተህ እንዲታጠቡ አድርጋቸው፤ እጠባቸው፤ 13የተቀደሱትን ልብሶች አልብሰህ በመቀባት አሮንን ለእኔ የተለየ ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ አድርገው። 14ልጆቹንም አምጥተህ ቀሚስ አልብሳቸው። 15እነርሱም ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ልክ አባታቸውን በቀባኸው ዐይነት ቀባቸው፤ በመቀባታቸውም ምክንያት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ካህናት ሆነው ያገለግሉኛል።”
16ሙሴም ልክ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሁሉን ነገር አደረገ። 17ስለዚህ ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ዓመት፥ የመጀመሪያው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን የመገናኛው ድንኳን ተተከለ። 18ሙሴ ድንኳኑን ተከለ፤ የድንኳኑን እግሮች አኖረ፤ ተራዳዎቹንና ምሰሶዎቹን አቆመ፤ መወርወሪያዎቹንም አያያዘ። 19እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ክዳኑን በድንኳኑ ላይ ዘረጋ፤ የውጪውንም ክዳን በላዩ አደረገ፤ 20ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች ወስዶ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ አስቀመጣቸው፤ መሎጊያዎችንም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ አስገባ፤ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ አኖረ፤ 21ታቦቱንም ወደ ድንኳኑ ውስጥ አስገባውና የሚከለልበትን መጋረጃ ሰቀለ፤ በዚህም ዐይነት ልክ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ታቦቱን ሸፈነው።
22ጠረጴዛውን ወደ ድንኳኑ ውስጥ አስገብቶ ከመጋረጃው ውጪ በስተ ሰሜን በኩል አስቀመጠው። 23እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የተቀደሰ ኅብስት በገበታው ላይ አሰናዳ። 24መቅረዙንም ወደ ድንኳኑ አስገብቶ ከገበታው ፊት ለፊት በድንኳኑ በደቡብ በኩል አስቀመጠው። 25እንዲሁም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በዚያ በእግዚአብሔር ፊት መብራቶቹን አበራ። #ዘፀ. 30፥11-16። 26የወርቁንም መሠዊያ ወደ ድንኳኑ አስገብቶ ከመጋረጃው ፊት ለፊት አኖረው። #ማቴ. 17፥24። 27እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን በላዩ ላይ አጠነ። 28መጋረጃውንም በድንኳኑ መግቢያ ደጃፍ ላይ ሰቀለ። 29እዚያም በድንኳኑ መግቢያ ፊት ለፊት የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ አኖረ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቊርባን እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በእርሱ ላይ አቀረበ፤ 30የመታጠቢያውንም ሳሕን በድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አስቀምጦ ውሃ ሞላበት። 31ሙሴ፥ አሮንና ልጆቹ እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በዚያ ታጠቡ፤ 32ወደ ድንኳኑ በሚገቡበትና ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ይህን ማድረግ ነበረባቸው። 33ሙሴ በድንኳኑና በመሠዊያው ዙሪያ የሚሆነውን ድንኳኑ ሠራ፤ ወደ ድንኳኑ በሚያስገባው ደጃፍ መጋረጃ ሰቀለ፤ በዚህም ዐይነት ሥራውን ሁሉ ፈጸመ።
የእግዚአብሔር ክብር
(ዘኍ. 9፥15-23)
34ከዚህ በኋላ ድንኳኑ በደመና ተሸፈነ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ድንኳኑን ሞላው። #1ነገ. 8፥10-11፤ ኢሳ. 6፥4፤ ሕዝ. 43፥4-5፤ ራዕ. 15፥8። 35ደመናው ስለረበበበትና የእግዚአብሔርም ክብር ድንኳኑን ስለ ሞላው ሙሴ ወደ ድንኳኑ ለመግባት አልቻለም። 36በጉዞአቸው ሁሉ እስራኤላውያን የሰፈሩበትን ቦታ ለቀው የሚንቀሳቀሱት ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሣበት ጊዜ ብቻ ነበር፤ 37ደመናው እዚያው እስካለ ድረስ ሰፈራቸውን ለቀው አይሄዱም ነበር። 38በሚጓዙበት ጊዜ ሁሉ በቀን የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጠው ደመና ድንኳኑን ሲሸፍን፥ በሌሊት ደግሞ በደመናው ውስጥ እሳት ያዩ ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in