YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6

6
ስለ ወላጆችና ስለ ልጆች
1ልጆች ሆይ! ተገቢ ነገር ስለ ሆነ በጌታ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ። #ቆላ. 3፥20። 2“አባትህንና እናትህን አክብር” የሚለው ትእዛዝ የተስፋ ቃል ያለበት የመጀመሪያ ትእዛዝ ነው፤ 3ይህንንም ብታደርግ “ሁሉ ነገር ይሰምርልሃል፤ በዚህም ምድር ላይ ዕድሜህ ይረዝማል።” #ዘፀ. 20፥12፤ ዘዳ. 5፥16።
4እናንተም ወላጆች ሆይ! በጌታ በኢየሱስ ሥነ ሥርዓትን በማስተማር፥ በማረምና በመገሠጽ አሳድጉአቸው እንጂ ልጆቻችሁን በማስቈጣት አታስመርሩአቸው። #ቆላ. 3፥22-25።
ስለ ጌቶችና ስለ አገልጋዮች
5እናንተ አገልጋዮች ሆይ! በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑት በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ታዘዙ፤ ለክርስቶስ በምታገለግሉት ዐይነት በልብ ቅንነት ታዘዙአቸው። 6የምትታዘዙትም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ እንደሚፈጽሙ እንደ ክርስቶስ አገልጋዮች ሆናችሁ ነው እንጂ ሰውን ደስ ለማሰኘት ብላችሁ ለታይታ አይሁን። 7ሰውን ሳይሆን ጌታን እንደምታገለግሉ አድርጋችሁ በመልካም ፈቃድ አገልግሉ። 8ባሪያም ሆነ ጌታ እያንዳንዱ በሠራው መልካም ሥራ ከጌታ ዋጋውን የሚቀበል መሆኑን ታውቃላችሁ።
9እናንተም ጌቶች ሆይ! ለሰው ፊት የማያዳላ የእናንተና የእነርሱ ጌታ በሰማይ እንዳለ በማስታወስ ዛቻችሁን ትታችሁ ለአገልጋዮቻችሁ መልካም አድርጉላቸው። #ዘዳ. 10፥17፤ ቆላ. 3፥25፤ 4፥1።
ከእግዚአብሔር የሚገኝ የጦር መሣሪያ
10በቀረውስ በጌታና በእርሱም ታላቅ ኀይል በርቱ፤ 11የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ ለመቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን የጦር መሣሪያ በሙሉ ልበሱ። 12የእኛ ውጊያ ከሰዎች ጋር ሳይሆን በዚህ በጨለማ ዘመን ከሚሠሩት ገዢዎች፥ ከባለ ሥልጣኖችና ከዚህ ዓለም ኀይሎችና ይህም ማለት በሰማይ ካሉት ከርኩሳን መናፍስት ሠራዊት ጋር ነው። 13ስለዚህ በክፉ ቀን የጠላትን ኀይል ለመቋቋም እንድትችሉና ሁሉንም ፈጽማችሁ ጸንታችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር መሣሪያ አንሡ!
14እንግዲህ እውነትን እንደ ዝናር በወገባችሁ ታጥቃችሁ፥ ጽድቅን እንደ ጥሩር ለብሳችሁ፥ #ኢሳ. 11፥5፤ 59፥17። 15የሰላምን ወንጌል እንደ ጫማ በእግሮቻችሁ ተጫምታችሁ በመዘጋጀት ቁሙ። #ኢሳ. 52፥7። 16ከዚህም ሁሉ በላይ እንደ እሳት የሚንበለበሉትን የዲያብሎስን ፍላጻዎች ሁሉ ማጥፋት የምትችሉበትን እምነት እንደ ጋሻ አንግቡ። 17መዳንን እንደ ራስ ቊር በራሳችሁ ላይ ድፉ፤ እንዲሁም ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን ሰይፍ ይኸውም የእግዚአብሔርን ቃል ያዙ። #ኢሳ. 59፥17። 18ዘወትር በመንፈስ ቅዱስ እየተመራችሁ ጸሎትንና ልመናን አቅርቡ። በዚህም መሠረት እግዚአብሔር ለቀደሳቸው ሰዎች ነቅታችሁና ተግታችሁ ጸልዩ። 19የወንጌልን ምሥጢር ያለ ፍርሀት እንድገልጥ በምናገርበት ጊዜ አስፈላጊውን ቃል እንዲሰጠኝ ለእኔም ጸልዩልኝ። 20አሁንም በሰንሰለት ታስሬ የዚሁ ወንጌል መልእክተኛ ነኝ፤ ስለዚህ እንደሚገባኝ ያለ ፍርሀት እንድናገር ጸልዩልኝ።
የመጨረሻ ሰላምታ
21የተወደደው ወንድማችንና በጌታ ኢየሱስ ሥራ ታማኝ አገልጋይ የሆነው ቲኪቆስ የእኔ ሁኔታ እንዴት እንደ ሆነና ምን እንደምሠራ ሁሉን ነገር ይነግራችኋል። #ሐ.ሥ. 20፥4፤ 2ጢሞ. 4፥12። 22ስለዚህ እኛ እንዴት እንደ ሆንን እንድታውቁና እናንተንም እንዲያበረታታችሁ በማለት እርሱን ወደ እናንተ ልኬዋለሁ። #ቆላ. 4፥7-8።
23ከእግዚአብሔር አብና ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን። 24በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in