ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3
3
የጳውሎስ ሥራ ለአሕዛብ
1ስለዚህ እኔ ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንኩት ለእናንተ ለአሕዛብ ስል ነው። 2ለእናንተ ጥቅም እንዳውለው እግዚአብሔር በጸጋው የአገልግሎት ዕድል እንደ ሰጠኝ በእርግጥ ሰምታችኋል። 3አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍኩላችሁ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ገልጦ በራእይ አሳይቶኛል። 4ይህን የጻፍኩላችሁንም ስታነቡ ስለ ክርስቶስ ምሥጢር እኔ ያስተዋልኩትን ለመረዳት ትችላላችሁ። 5ይህም ምሥጢር በእግዚአብሔር መንፈስ ለቅዱሳን ሐዋርያቱና ነቢያቱ አሁን እንደተገለጠው ዐይነት ባለፉት ዘመናት ለነበሩት ሰዎች አልተገለጠም። 6ይህም የሚያመለክተው አሕዛብ ከአይሁድ ጋር የርስቱ ወራሾችና የአንድ አካል ክፍሎች ሆነው እግዚአብሔር ለሰጠው ተስፋ በወንጌል አማካይነት በኢየሱስ ክርስቶስ ተካፋዮች መሆናቸውን ነው። #ቆላ. 1፥26-27።
7እግዚአብሔር በኀይሉ አሠራር በሰጠኝ የጸጋ ስጦታ እኔም የዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆኜአለሁ። 8እኔ ከቅዱሳን ሁሉ የማንስ ብሆንም እንኳ ወሰን የሌለውን የክርስቶስን ባለጸግነት ለአሕዛብ እንዳበሥር በእግዚአብሔር ጸጋ ይህ ዕድል ተሰጠኝ። 9እንዲሁም ባለፉት ዘመናት ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ተሰውሮ ስለ ነበረው ምሥጢር የእግዚአብሔር ዕቅድ ምን እንደ ሆነ ለሁሉ እንድገልጥ ጸጋ ተሰጠኝ። 10ይህም የሆነው በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት በሰማይ ያሉት አለቆችና ባለሥልጣኖች የእግዚአብሔርን ጥበብ በየመልኩ እንዲያውቁ ነው። 11እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የፈጸመው በዘለዓለማዊው ዕቅዱ መሠረት ነው። 12የክርስቶስ በመሆናችንና በእርሱ በማመናችን በእግዚአብሔር ፊት በድፍረትና በመተማመን መቅረብ እንችላለን። 13እኔ ስለ እናንተ የምቀበለው መከራ ክብራችሁ ነው፤ ስለዚህ በመከራዬ ምክንያት ተስፋ አትቊረጡ ብዬ እለምናችኋለሁ።
የክርስቶስ ፍቅር
14እንግዲህ በእግዚአብሔር አብ ፊት በጒልበቴ ተንበርክኬ የምጸልየው በዚህ ምክንያት ነው። 15በሰማይና በምድር ያለ እያንዳንዱ ቤተሰብ እውነተኛ ስሙን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ነው። 16እግዚአብሔር ውስጣዊውን ሰውነታችሁን የሚያጠነክር ኀይል በመንፈሱ አማካይነት ከክብሩ ባለጸግነት እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ። 17እንዲሁም ክርስቶስ በእምነት በልባችሁ እንዲኖርና እናንተም ሥር ሰዳችሁ በፍቅር የጸናችሁ እንድትሆኑ እጸልያለሁ። 18ደግሞም የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱና ርዝመቱ፥ ከፍታውና ጥልቀቱ፥ ምን ያኽል መሆኑን ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ማስተዋል እንድትችሉና 19ይህን ከሰው ዕውቀት በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር እንድታውቁ በእግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ለመሞላትም እንድትበቁ እጸልያለሁ።
20ስለዚህ በእኛ ውስጥ በሚሠራው ኀይሉ አማካይነት ከምንለምነውና ከምናስበው በላይ እጅግ አትረፍርፎ ሊያደርግ ለሚቻለው አምላክ፥ 21ለእርሱ በቤተ ክርስቲያንና በኢየሱስ ክርስቶስ በዘመናት ሁሉ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
Currently Selected:
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997