YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ዳንኤል 1

1
ዳንኤልና ጓደኞቹ በናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት
1ኢዮአቄም በይሁዳ ላይ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት። #2ነገ. 24፥1፤ 2ዜ.መ. 36፥5-7። 2እግዚአብሔር የይሁዳን ንጉሥ ኢዮአቄምንና የቤተ መቅደሱንም ንዋያተ ቅድሳት በከፊል ለናቡከደነፆር አሳልፎ ሰጣቸው፤ ንጉሡም ንዋያተ ቅድሳቱን በባቢሎን ባሉት የጣዖት አማልክቱ ቤተ መቅደስ ውስጥ አኖረ።
3ከዚህ በኋላ ንጉሥ ናቡከደነፆር አሽፈናዝ የተባለውን የባለሟሎቹን አለቃ ከእስራኤል ምርኮኞች መካከል የንጉሣዊ ቤተሰቦችና የመሳፍንት ልጆች ከሆኑት ወጣቶች መካከል ጥቂቶቹን መርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ 4የሚመረጡትም ወጣቶች በቤተ መንግሥት ለማገልገል በቂ ችሎታ እንዲኖራቸው፥ መልከ መልካሞች፥ ጥበብን ሁሉ ማስተዋልና ሁሉን ነገር በፍጥነት መረዳት የሚችሉ፥ የአካል ጒድለት የሌለባቸው መሆን ይገባቸዋል፤ እንዲሁም የባቢሎናውያንን ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ያስተምራቸውም ዘንድ አዘዘው። #2ነገ. 20፥17-18፤ 24፥10-16፤ 2ዜ.መ. 36፥10፤ ኢሳ. 39፥7-8። 5ምግባቸውና የሚጠጡት የወይን ጠጅ ከንጉሡ ማእድ እንዲሆን ታዘዘላቸው፤ በዚህ ዐይነት ለሦስት ዓመት ከሠለጠኑ በኋላ በንጉሡ ፊት ቀርበው የቤተ መንግሥት ሥራቸውን እንዲጀምሩ ተወሰነ። 6ከተመረጡትም መካከል ነገዳቸው ከይሁዳ ወገን የሆነ ዳንኤል፥ ሐናንያ፥ ሚሳኤልና ዐዛርያ ነበሩ። 7የንጉሡም ባለሟሎች አለቃ ስማቸውን በመለወጥ ዳንኤልን ብልጣሶር፤ ሐናንያን ሲድራቅ፤ ሚሳኤልን ሚሳቅ፤ ዐዛርያን አብደናጎ ብሎ ጠራቸው።
8ዳንኤል ከንጉሡ ምግብ በመመገብና የወይን ጠጁንም በመጠጣት ራሱን ላለማርከስ ወሰነ፤ በዚህም ሐሳብ እንዲስማማለት አሽፈናዝን ለመነው። 9እግዚአብሔርም ለዳንኤል በሹሙ ፊት ሞገስን ሰጥቶ ልቡን አራራለት። 10ይሁን እንጂ ንጉሡን ስለ ፈራ አሽፈናዝ ዳንኤልን “ምግባችሁንና መጠጣችሁን ያዘዘ ንጉሡ ራሱ ነው፤ እናንተ ከሌሎቹ ወጣቶች ይልቅ ከስታችሁና ተጐሳቊላችሁ ብትገኙ ጌታዬ ንጉሡ በሞት ይቀጣኛል ብዬ እፈራለሁ” አለው።
11ከዚህ በኋላ ዳንኤል ራሱንና ጓደኞቹን ሐናንያን፥ ሚሳኤልንና አዛርያን እንዲጠብቅ አሽፈናዝ ወደ መደበው ጠባቂ ሄዶ እንዲህ አለው፤ 12“አትክልት እየተመገብንና ውሃ እየጠጣን እንድንቈይ በማድረግ እኛን አገልጋዮችህን ለዐሥር ቀን ያኽል ፈትነን፤ 13ከዚያ በኋላ የእኛን ሁኔታ ከቤተ መንግሥት የታዘዘውን ምግብ ከሚመገቡ ወጣቶች ጋር ታስተያየዋለህ፤ በምታገኘውም ግንዛቤ መሠረት እኛን አገልጋዮችህን በተመለከተ የመሰለህን ታደርጋለህ።”
14ጠባቂውም በዚህ ሐሳብ ተስማምቶ ለዐሥር ቀን ፈተናቸው። 15ዐሥሩም ቀን ከተፈጸመ በኋላ ከንጉሡ ምግብ ከሚመገቡት ወጣቶች ሁሉ ይልቅ እነርሱ ፊታቸው አምሮ፥ ሰውነታቸው ወፍሮ ተገኙ። 16ከዚያን ጊዜ አንሥቶ ጠባቂው ከቤተ መንግሥት የሚላክላቸውን ምርጥ ምግብና የወይን ጠጅ አስቀርቶ ለእነርሱ የአትክልት ምግብ ይሰጣቸው ጀመር።
17እግዚአብሔርም ለእነዚህ ለአራት ወጣቶች በማናቸውም ጥበብና ሥነ ጽሑፍ ዕውቀትና ማስተዋል ሰጣቸው፤ ዳንኤል ግን በተጨማሪ ራእይንና ሕልምን የመተርጐም ችሎታ ነበረው።
18ንጉሡ የወሰነው ሦስት ዓመት ሲፈጸም አሽፈናዝ ወጣቶቹን ሁሉ ወስዶ በናቡከደነፆር ፊት አቀረባቸው። 19ንጉሡ ሁሉንም ባነጋገራቸው ጊዜ ከእነርሱ መካከል ዳንኤልን፥ ሐናንያን፥ ሚሳኤልንና ዐዛርያን የሚወዳደር አልተገኘም፤ ስለዚህ እነርሱ በንጉሡ ፊት እንዲያገለግሉ ተመረጡ። 20ጥበብና ማስተዋልን በተመለከቱ ጉዳዮች ንጉሡ በሚጠይቃቸው ነገሮች በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ከሚገኙ ጠንቋዮችና አስማተኞች ሁሉ ዐሥር ጊዜ ብልጫ ያላቸው ሆነው አገኛቸው። 21በዚህ ዐይነት ዳንኤል ቂሮስ እስከ ነገሠበት መጀመሪያ ዓመት ድረስ በቤተ መንግሥት ውስጥ ማገልገሉን ቀጠለ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in