YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ አሞጽ 6

6
የእስራኤል መቀጣት
1የእስራኤል ሕዝብ ርዳታቸውን ፈልጎ ወደ መሪዎቹ ይመጣል፤ እነርሱ ግን በጽዮን ተዝናንተው ስለሚቀመጡና በሰማርያ ተራራ ላይ ያለ ሥጋት ስለሚኖሩ ለእነዚህ ታዋቂ መሪዎች ወዮላቸው! 2እስቲ ወደ ካልኔ ከተማ ሄዳችሁ ተመልከቱ፤ ከዚያም አልፋችሁ “ሐማት” ተብላ ወደምትጠራው ታላቂቱ ከተማና የፍልስጥኤማውያን ከተማ ወደሆነችው ወደ ጋት ውረዱ፤ እናንተ ከእነርሱ ትበልጣላችሁን? ግዛታችሁስ ከእነርሱ ግዛት ይበልጣልን? 3እናንተ “ክፉ ቀን ፈጥኖ አይመጣም” ብላችሁ በማሰብ በአስተዳደራችሁ የግፍን ሥራ ታፋጥናላችሁ። 4ከዝሆን ጥርስ በተሠሩ አልጋዎች ላይ ትተኛላችሁ፤ ከበግ መንጋ የጠቦት ሥጋ፥ ከከብት መንጋ የጥጃ ሥጋ እየበላችሁ በድንክ አልጋ ላይ ታርፋላችሁ! 5የሙዚቃ ቃና በመቃኘት በበገና የማይረባ ዘፈን ትዘፍናላችሁ፤ እንደ ዳዊትም ቅኔዎችን በማዘጋጀት በሙዚቃ መሣሪያ ታዜማላችሁ። 6የወይን ጠጁን በብርሌ ሳይሆን በገምቦ ትጠጣላችሁ፤ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቶ ትቀባላችሁ፤ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ስለ ደረሰው ጥፋት ግን ፈጽሞ አታዝኑም፤ ይህን ሁሉ ስለምታደርጉ ወዮላችሁ! 7ስለዚህ ተማርካችሁ በመሄድ እናንተ የመጀመሪያዎቹ ትሆናላችሁ፤ በዚያን ጊዜ የዚያ የቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ ኑሮአችሁ ፍጻሜ ይሆናል።
8የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር “የእስራኤልን ሕዝብ ትዕቢት ጠልቼአለሁ፤ የተዋቡ ቤተ መንግሥቶቻቸውን ተጸይፌአለሁ፤ ከዚህም የተነሣ ከተማይቱንና በእርስዋ የሚኖሩትን ሁሉ ለጠላት አሳልፌ እሰጣለሁ” ሲል በራሱ ምሎአል።
9ከአንድ ቤተሰብ ዐሥር ሰዎች ቢቀሩ እነርሱም እንኳ ይሞታሉ፤ 10ከሟቾቹ የአንዱ የቅርብ ዘመድ የሆነና ሥርዓተ ቀብሩን የሚፈጽም ሬሳውን ከቤት አውጥቶ ይወስዳል፤ በዚያን ጊዜ በቤት ውስጥ ያለውን አንድ ሰው ጠርቶ “ከአንተ ጋር የቀረ ሌላ ሰው አለን?” ብሎ ይጠይቀዋል፤ ሰውየውም “ማንም የቀረ የለም!” ብሎ ይመልስለታል፤ ጠያቂውም “የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ስለማይገባን ዝም በል!” ይለዋል።
11በእግዚአብሔር ትእዛዝ ታላላቅ ቤቶች ይፈርሳሉ፤ ታናናሽ ቤቶችም የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ። 12ፈረሰኛ በቋጥኝ ላይ ሊጋልብ ይችላልን? ገበሬስ በባሕር ላይ በሬ ጠምዶ ማረስ ይችላልን? እናንተ ግን ፍርድን ወደ መርዝ ለወጣችሁ፤ እውነትንም እንደ ሬት መራራ አደረጋችሁ።
13ሎደባር የምትባለውን ከተማ በማሸነፋችሁ ተደስታችኋል፤ “ቃርናይም የምትባለውንም ከተማ በጒልበታችን ይዘናል” ብላችሁ ትፎክራላችሁ። #6፥13 ሎደባር፦ የከተማው ስም ሲሆን ቃሉ በዕብራይስጥ “ከንቱ ነገር” ማለት ነው። #6፥13 ቃርናይም፦ የትንሽ ከተማ ስም በዕብራይስጥ ቀንድ ማለት ሲሆን የኀይል ምሳሌ ነው።
14የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በእናንተ ላይ የሌላ ሕዝብ ኀይል አስነሣባችኋለሁ፤ እርሱም በሰሜን ከሐማት መግቢያ በር ጀምሮ በደቡብ እስከ አረባ ሸለቆ ድረስ ዘልቆ ያስጨንቃችኋል።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in