YouVersion Logo
Search Icon

የሐዋርያት ሥራ 11

11
ጴጥሮስ ወደ አሕዛብ ለምን እንደ ሄደ ማስረዳቱ
1በይሁዳ ምድር የሚገኙ ሐዋርያትና ወንድሞች አሕዛብ የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላቸውን ሰሙ። 2ጴጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ በሄደ ጊዜ በግዝረት አስፈላጊነት የሚያምኑ የአይሁድ ክርስቲያኖች፥ 3“ስለምን ወዳልተገረዙ ሰዎች ቤት ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ?” በማለት ወቀሱት። 4ጴጥሮስ ግን እንዲህ ሲል ሁሉንም ነገር በተከታታይ ማስረዳት ጀመረ፦
5“እኔ በኢዮጴ ከተማ በጸሎት ላይ ሳለሁ በተመስጦ ራእይ አየሁ፤ ያየሁትም ትልቅ የመጋረጃ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራት ማእዘን ተይዞ ከሰማይ ሲወርድና ወደ እኔ ሲመጣ ነው፤ 6እርሱን ትኲር ብዬ ስመለከት በመጋረጃው ጨርቅ ላይ እንስሶችን፥ የዱር አራዊትን፥ በልባቸው የሚሳቡ ፍጥረቶችንና በሰማይ የሚበርሩ ወፎችን አየሁ፤ 7‘ጴጥሮስ ሆይ! ተነሥና እያረድክ ብላ!’ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ፤ 8እኔ ግን ‘አይሆንም ጌታ ሆይ! ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ነገር በአፌ ገብቶ አያውቅም’ አልኩ። 9ነገር ግን ሁለተኛ ጊዜ፥ ‘እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ ርኩስ ነው ማለት አይገባህም’ የሚል መልስ ከሰማይ ሰማሁ። 10ይህም ሦስት ጊዜ ከሆነ በኋላ ያ ጨርቅ የሚመስል ነገር በሙሉ ወደ ሰማይ ተወሰደ። 11እነሆ፥ በዚያን ጊዜ ከቂሳርያ ወደ እኔ የተላኩ ሦስት ሰዎች እኔ ወደነበርኩበት ቤት ደረሱ። 12ያላንዳች ማመንታት ከእነርሱ ጋር እንድሄድም መንፈስ ቅዱስ ነገረኝ፤ እነዚህ ስድስት ወንድሞችም ከእኔ ጋር ነበሩ፤ ከእነርሱም ጋር አብረን ቆርኔሌዎስ ወደ ተባለው ሰው ቤት ገባን። 13እርሱም መልአክን በቤቱ ውስጥ ቆሞ እንዳየና ‘ወደ ኢዮጴ ሰው ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ 14እርሱ አንተና ቤተሰብህ ሁሉ የምትድኑበትን ቃል ይነግርሃል’ እንዳለው ነገረን። 15እኔም መናገር በጀመርኩ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ዐይነት በእነርሱ ላይ ወረደ። 16በዚያን ጊዜ ‘ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’ በማለት ጌታ የተናገረውን ቃል አስታወስኩ። #ሐ.ሥ. 1፥5። 17እኛ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ባመንን ጊዜ እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠውን ስጦታ ለእነርሱም ከሰጣቸው፤ ታዲያ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል የምችል እኔ ማን ነኝ!”
18እነርሱም ይህንን በሰሙ ጊዜ የሚመልሱትን አጥተው ዝም አሉ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔር ለአሕዛብም ለአዲስ ሕይወት የሚያበቃቸውን ንስሓ ሰጥቶአቸዋል፤” በማለትም እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
አማኞች በአንጾኪያ “ክርስቲያን” መባላቸው
19እስጢፋኖስ ተወግሮ በሞተ ጊዜ በተነሣው ስደት ምክንያት የተበተኑት አማኞች እስከ ፊንቄና እስከ ቆጵሮስ እስከ አንጾኪያም ሄዱ፤ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለሌሎች አይናገሩም ነበር። #ሐ.ሥ. 8፥1-4። 20ይሁን እንጂ ከቆጵሮስና ከቀሬና የመጡ አንዳንድ አማኞች ወደ አንጾኪያ በሄዱ ጊዜ ለግሪኮች ጭምር ስለ ጌታ ኢየሱስ መልካም ዜናን አበሠሩ። 21ጌታም በኀይሉ ይረዳቸው ነበር፤ ብዙ ሰዎችም አምነው ወደ ጌታ ተመለሱ።
22በኢየሩሳሌም የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ይህን ስለ ሰማች በርናባስን ወደ አንጾኪያ ላከችው። 23እርሱም ሄዶ እግዚአብሔር ጸጋውን ለሕዝቡ እንዴት እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ ደስ አለው፤ ሁሉም በሙሉ ልብ ጸንተው ለጌታ ታማኞች ሆነው እንዲኖሩም መከራቸው። 24እርሱ መንፈስ ቅዱስና እምነት የሞላበት ደግ ሰው ስለ ነበረ ቊጥራቸው ብዙ የሆኑ ሰዎች ወደ ጌታ ተመለሱ።
25ከዚህ በኋላ በርናባስ ሳውልን ለመፈለግ ወደ ጠርሴስ ሄደ። 26ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው፤ ሁለቱም አንድ ዓመት ሙሉ ከቤተ ክርስቲያን ጋር በአንድነት ሆነው ብዙ ሰዎችን አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ “ክርስቲያን” ተብለው ተጠሩ።
27በዚያን ጊዜ አንዳንድ ነቢያት ተብለው የሚጠሩ መምህራን ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ 28ከእነርሱም አንዱ አጋቦስ የሚባለው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ እንደሚሆን በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነት ትንቢት ተናገረ፤ ይህም የሆነው በሮም ንጉሠ ነገሥት በቀላውዴዎስ ዘመን ነበር። #ሐ.ሥ. 21፥10። 29ስለዚህ በአንጾኪያ የሚኖሩ ምእመናን በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች እያንዳንዳቸው እንደየችሎታቸው በማዋጣት ርዳታ እንዲላክ ወሰኑ። 30መዋጮም አድርገው በበርናባስና በሳውል እጅ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላኩ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in