ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 3
3
በእስራኤልና በሞአብ መካከል የተደረገ ጦርነት
1የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ዐሥራ ሁለት ዓመት ገዛ፤ 2እርሱም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ ይሁን እንጂ እርሱ የአባቱንና የእናቱን የኤልዛቤልን ያኽል መጥፎ ሰው አልነበረም፤ ባዓል ተብሎ የሚጠራውን ባዕድ አምላክ ለማምለክ አባቱ አሠርቶት የነበረውን ምስል አስወገደ፤ 3ይህም ሆኖ ከእርሱ በፊት እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራው የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን አምልኮ ተከተለ እንጂ አላስወገደውም።
4የሞአብ ንጉሥ ሜሻዕ በግ አርቢ ነበር፤ በየዓመቱም አንድ መቶ ሺህ ጠቦትና የአንድ መቶ ሺህ በጎች ጠጒር ለእስራኤል ንጉሥ ይገብር ነበር፤ 5ነገር ግን የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በሞተ ጊዜ የሞአብ ንጉሥ ሜሻዕ በእስራኤል ላይ ዐመፀ። 6በዚያን ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም ወዲያውኑ ከሰማርያ ወጥቶ ወታደሮቹን ሁሉ በአንድነት ሰበሰበ፤ 7ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ኢዮሣፍጥም “የሞአብ ንጉሥ በእኔ ላይ አምፆብኛል፤ በእርሱ ላይ በማደርገው ጦርነት ከእኔ ጋር ትተባበራለህን?” የሚል መልእክት ላከ።
ንጉሥ ኢዮሣፍጥም “አዎ እተባበርሃለሁ፤ እኔን እንደ አንተ፥ ሠራዊቴን እንደ ሠራዊትህ፥ ፈረሶቼን እንደ ፈረሶችህ መቊጠር ትችላለህ” ሲል ከመለሰ በኋላ፥ 8ዳሩ ግን “አደጋ ለመጣል የምንጓዘው በየትኛው መንገድ ነው?” ሲል ጠየቀው።
ንጉሥ ኢዮራምም “በኤዶም በረሓ የሚገኘውን ዙሪያ መንገድ ይዘን እንጓዛለን” ሲል መለሰለት።
9ስለዚህም ንጉሥ ኢዮራምና እንዲሁም የይሁዳና የኤዶም ነገሥታት ለዘመቻ ወጡ፤ ከሰባት ቀን ጒዞም በኋላ ውሃ አለቀባቸው፤ ለሠራዊቱም ሆነ ለጭነት እንስሶች ምንም ውሃ አልነበረም። 10ንጉሥ ኢዮራምም “እግዚአብሔር ሦስታችንንም ነገሥታት ለሞአብ ንጉሥ አሳልፎ ሊሰጠን ነውና ወዮልን!” ሲል ጮኸ።
11ንጉሥ ኢዮሣፍጥም “በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔርን መጠየቅ እንድንችል በዚህ አንድም ነቢይ የለምን?” ሲል ጠየቀ።
ከንጉሥ ኢዮራም ሠራዊት አዛዦች አንዱ፥ “ቀድሞ የኤልያስ ረዳት የነበረው የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ እዚህ አለ” ሲል መልስ ሰጠ።
12ንጉሥ ኢዮሣፍጥም “የእግዚአብሔር ቃል በእርሱ ዘንድ ይገኛል” አለ፤ ከዚያም በኋላ ሦስቱም ነገሥታት ወደ ኤልሳዕ ሄዱ።
13ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ ኢዮራምን፥ “እኔ አንተን የምረዳህ ስለምንድን ነው? ሄደህ አባትህና እናትህ ይጠይቁአቸው የነበሩትን እነዚያን ነቢያት ጠይቅ!” አለው።
ንጉሥ ኢዮራምም መልሶ፥ “አይደለም እኮ! ሦስታችንንም ነገሥታት ለሞአብ ንጉሥ አሳልፎ ለመስጠት የጠራን እግዚአብሔር ነው” አለ።
14ኤልሳዕም “እኔ በማገለግለው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! አንተን ለመርዳት ለመጣው ለይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ክብር ስል ነው እንጂ፥ ለአንተስ ምንም ነገር ላደርግልህ ባልተገባ ነበር፤ 15አሁንም በገና የሚደረድር ሰው አምጡልኝ” አለ።
ባለ በገናውም በሚደረድርበት ጊዜ የእግዚአብሔር ኀይል በኤልሳዕ ላይ ወርዶ እንዲህ አለ፤ 16“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘በዚህ የደረቀ ሸለቆ ሁሉ የውሃ ጒድጓድ ቆፍሩ፤ 17ምንም ዝናብና ነፋስ ባታዩም፥ ይህ ሸለቆ በውሃ የተሞላ ይሆናል፤ እናንተ፥ የቀንድ ከብቶቻችሁና የጭነት እንስሶቻችሁ ሁሉ የምትጠጡት በቂ ውሃ ታገኛላችሁ።’ 18ነገር ግን ይህን ማድረግ በእግዚአብሔር ዘንድ ቀላል ነገር ነው፤ ከዚህም በላይ እርሱ በሞአባውያን ላይ ድልን ያጐናጽፋችኋል። 19የተመሸጉና ምርጥ የሆኑ ከተሞቻቸውን ሁሉ ድል አድርጋችሁ ትይዛላችሁ፤ የፍራፍሬ ዛፎቻቸውን ሁሉ ትቈርጣላችሁ፤ ምንጮቻቸውን ትደፍናላችሁ፤ ለም የሆኑ የእርሻ ቦታዎቻቸውን በማበላሸት ድንጋይ ትከምሩባቸዋላችሁ።”
20በማግስቱም ጠዋት መሥዋዕት የሚቀርብበት ሰዓት ሲደርስ ከኤዶም በኩል የውሃ ምንጭ ፈልቆ ምድሩን ሸፈነው።
21ሞአባውያንም ሦስቱ ነገሥታት አደጋ ሊጥሉባቸው መምጣታቸውን በሰሙ ጊዜ፥ ከሽማግሌ እስከ ወጣት መሣሪያ መያዝ የሚችሉ ሰዎች ሁሉ ተጠርተው በመውጣት በጠረፉ ላይ ተጠባበቁ። 22በማግስቱም ጠዋት ከእንቅልፋቸው ነቅተው ሲመለከቱ፥ በውሃው ላይ የሚያበራው የፀሐይ ነጸብራቅ እንደ ደም መስሎ ታያቸው፤ 23ስለዚህም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ “ይህ ነገር ደም ነው! የሦስቱ ጠላቶቻችን ሠራዊቶች እርስ በርሳቸው በመተራረድ ተላልቀዋል! እንግዲህ ሄደን ሰፈራቸውን እንዝረፍ!” ተባባሉ።
24ነገር ግን እነርሱ ወደ ሰፈር በደረሱ ጊዜ እስራኤላውያን ተነሥተው አደጋ በመጣል ወደ ኋላ መለሱአቸው፤ እስራኤላውያን አገሪቱን ወረው ሞአባውያንን ጨፈጨፉአቸው። 25ከተሞቻቸውን ደመሰሱ፤ ለም በሆነው እርሻ ውስጥ በሚያልፉበትም ጊዜ እያንዳንዱ እስራኤላዊ አንዳንድ ድንጋይ ይወረውርበት ስለ ነበር በመጨረሻ እርሻዎቹ ሁሉ በድንጋይ ተሸፈኑ፤ ምንጮቻቸውን ደፈኑ፤ የፍራፍሬ ዛፎቻቸውንም ሁሉ ቈረጡ፤ በመጨረሻም የአገሪቱ ዋና ከተማ የነበረችው ቂርሔሬስ ብቻ ቀረች፤ እርስዋንም ድንጋይ የሚያወነጭፉ ጦረኞች ከበው አደጋ ጣሉባት።
26የሞአብ ንጉሥ ድል እንደ ተመታ ባረጋገጠ ጊዜ ሰይፍ የታጠቁ ሰባት መቶ ሰዎችን አስከትሎ የጠላት ጦር የተሰለፈበትን መስመር ጥሶ ለማምለጥና ወደ ሶርያ ንጉሥ ለመሄድ ቢሞክርም ከቶ አልተሳካለትም። #3፥26 ሶርያ፦ ወይም ኤዶም 27ስለዚህም በእርሱ ምትክ መንገሥ የሚገባውን የመጀመሪያ ልጁን በከተማይቱ ግንብ ላይ ለሞአብ አምላክ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እስራኤላውያንም በነገሩ ስለ ተሠቀቁ ከተማይቱን ለቀው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 3: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997