2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10
10
ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ የሰጠው መከላከያ መልስ
1እኔ ጳውሎስ በእናንተ ፊት ሳለሁ ትሑት ተባልኩ፤ ከእናንተ ስርቅ ግን በእናንተ ላይ ደፋር ተባልኩ፤ በክርስቶስ ቸርነትና ደግነት እለምናችኋለሁ፤ 2የምለምናችሁም ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ በድፍረት እንድናገር እንዳታደርጉኝ ነው፤ በሥጋ አስተሳሰብ እንደምንመላለስ አድርገው በሚገምቱን በአንዳንድ ሰዎች ፊት ግን በድፍረት ለመናገር እፈልጋለሁ። 3ምንም እንኳ በዓለም ብንኖር የምንዋጋው ዓለማዊ ጦርነት አይደለም። 4የጦር መሣሪያዎቻችንም ምሽግ ለማፍረስ የሚያስችል መለኮታዊ ኀይል ያላቸው ናቸው እንጂ ዓለማዊ የጦር መሣሪያዎች አይደሉም። 5እግዚአብሔርን በማወቅ ላይ እንቅፋት ሆነው የሚነሡትን ክርክርና ትዕቢት እናፈርሳለን፤ የሰውን ሐሳብ ሁሉ እየማረክንም ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን። 6የእናንተ ታዛዥነት ፍጹም ሲሆን ማንኛውንም አለመታዘዝ ለመቅጣት ዝግጁዎች እንሆናለን።
7እናንተ የምትመለከቱት በውጪ የሚታየውን ነገር ብቻ ነው፤ ማንም ሰው የክርስቶስ ነኝ ብሎ ቢተማመን እንደገና ያስብበት፤ እኛም እንደ እርሱ የክርስቶስ መሆናችንን ይገንዘብ። 8ጌታ ስለ ሰጠን ሥልጣን በጣም ብመካም አላፍርበትም፤ ይህ ሥልጣን የተሰጠን እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ አይደለም። 9በመልእክቴ የማስፈራራችሁ አይምሰላችሁ። 10ምናልባት አንዳንዶች “የጳውሎስ መልእክቶች ከባዶችና ብርቱዎች ናቸው፤ እርሱ ራሱ ከእኛ ጋር ሲሆን ግን ደካማ ነው፤ ንግግሩም የተናቀ ነው” ይሉ ይሆናል። 11ይህን የሚሉ ሰዎች እኛ በሩቅ ሆነን በመልእክቶቻችን በምንጽፈውና በቅርብም ከእናንተ ጋር ሆነን በምንሠራው መካከል ምንም ልዩነት አለመኖሩን ይገንዘቡ።
12ይሁን እንጂ ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ራሳችንን ልናወዳድር ወይም ራሳችንን ልናነጻጽር አንደፍርም፤ እነርሱ ግን ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር በማመዛዘናቸውና ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር በማወዳደራቸው አስተዋዮች አይደሉም። 13እኛ ግን እስከ እናንተም እንኳ እስክንደርስ እግዚአብሔር በሰጠን የሥራ ክልል እንመካለን እንጂ ከመጠን በላይ የምንመካ አይደለንም። 14እናንተም ያላችሁት በሥራችን ክልል ውስጥ ስለ ሆነ የክርስቶስን ወንጌል ለማስተማር ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ ከዚያ ክልል አላለፍንም። 15ስለዚህ እግዚአብሔር ለእኛ ከወሰነልን ክልል አልፈን በሌሎች ሥራ ያለ ልክ አንመካም፤ ይልቅስ እምነታችሁ እንዲያድግና የእኛም ሥራ እግዚአብሔር በወሰነልን ክልል በእናንተ መካከል ይበልጥ እንዲስፋፋ ተስፋ እናደርጋለን። 16እንግዲህ በሌላው ሰው የሥራ ክልል ውስጥ ገብተን አስቀድሞ በተሠራው ሥራ ሳንመካ ከእናንተ ወዲያ ባሉት አገሮች የምሥራቹን ቃል ለማብሠር እንችላለን።
17ነገር ግን “የሚመካ በጌታ ይመካ።” #ኤር. 9፥24። 18ሰው ለመመስገን የሚበቃው ጌታ ሲያመሰግነው ነው እንጂ ራሱን በራሱ ሲያመሰግን አይደለም።
Currently Selected:
2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997