ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 21
21
1ኢዮሣፍጥ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮራም ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮራም
(2ነገ. 8፥17-24)
2የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጅ የሆነው ኢዮራም ስድስት ወንድሞች ነበሩት፤ እነርሱም ዐዛርያስ፥ ይሒኤል፥ ዘካርያስ፥ ዐዛርያ፥ ሚካኤልና ሸፋጥያ ተብለው የሚጠሩ ናቸው። 3አባታቸው ብዙ ወርቅና ብር እንዲሁም ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ሌላም ልዩ ልዩ ንብረት ሰጣቸው፤ በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች እያንዳንዱን በአንዳንድ ከተማ ላይ ሾመ፤ ኢዮራም የበኲር ልጁ ስለ ሆነ አባቱ ኢዮሣፍጥ በእርሱ እግር ተተክቶ እንዲነግሥ አደረገ፤ 4ኢዮራም መንግሥቱን ካጠናከረ በኋላ ወንድሞቹን በሙሉ እንዲሁም አንዳንድ የእስራኤል ባለሥልጣኖችን ገደለ።
5ኢዮራም በሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ስምንት ዓመት ገዛ፤ 6ከአክዓብ ሴቶች ልጆች አንዲቱን በማግባቱ፥ የንጉሥ አክዓብንና የሌሎቹን የእስራኤል ነገሥታት መጥፎ ምሳሌነት ተከትሎ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ሠራ፤ 7ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የዳዊትን ሥርወ መንግሥት ሊያጠፋ አልፈለገም፤ ይህም የሆነው እግዚአብሔር ቀደም ብሎ ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ስለ ነበርና የዳዊት ዘሮችም ዘወትር ሳያቋርጡ የሚነግሡ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የተስፋ ቃል ሰጥቶት ስለ ነበር ነው። #1ነገ. 11፥36።
8በኢዮራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐምፆ የራሱን ነጻ መንግሥት አቋቋመ፤ #ዘፍ. 27፥40። 9ስለዚህ ኢዮራም የጦር መኰንኖቹንና ሠረገሎቹን ይዞ በመዝመት ኤዶምን ወረረ፤ በዚያም የኤዶም ሠራዊት እነርሱን ከበባቸው፤ ነገር ግን ኢዮራምና ሠራዊቱ በሌሊት ከበባውን ጥሰው ለማምለጥ ቻሉ፤ 10ንጉሥ ኢዮራም የቀድሞ አባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኤዶም ከይሁዳ በመገንጠል ነጻ መንግሥት ሆነች፤ በዚሁ ወቅት የሊብና ከተማም በይሁዳ ላይ ዐመፀች፤ 11እርሱ በይሁዳ ኰረብቶች ላይ ሳይቀር እንኳ የአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎችን ሠራ፤ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ወደ ኃጢአት በመምራት እግዚአብሔርን እንዲያሳዝኑ አደረገ።
12ከዚህ በኋላ ነቢዩ ኤልያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢዮራም ላከ፦ “የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአባትህን የንጉሥ ኢዮሣፍጥን ወይም የአያትህን የንጉሥ አሳን መልካም ምሳሌነት አልተከተልክም፤ 13ነገር ግን የእስራኤልን ነገሥታት መጥፎ ምሳሌነት ተከተልክ፤ ልክ አክዓብና በእርሱ እግር የተተኩት ነገሥታት የእስራኤልን ሕዝብ በእግዚአብሔር እንዳይታመኑ እንዳደረጉት ሁሉ አንተም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ለእግዚአብሔር ታማኞች እንዳይሆኑ አደረግህ፤ ከአንተ የተሻሉትን የአባትህን ቤት ወንድሞችህን እንኳ ሳይቀር ገደልካቸው፤ 14ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሕዝብህን፥ ልጆችህንና ሚስቶችህን በብርቱ ይቀጣል፤ ንብረትህንም ሁሉ ያጠፋል፤ 15አንተም ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀትህ እስኪወጣ ድረስ በማይድን ክፉ የአንጀት በሽታ ትሠቃያለህ።”
16በባሕር ዳርቻ ሰፍረው በነበሩት ኢትዮጵያውያን አጠገብ ፍልስጥኤማውያንና ዐረቦች ይኖሩ ነበር፤ እግዚአብሔርም እነርሱን በኢዮራም ላይ ጦርነት እንዲያደርጉ አነሣሣቸው፤ 17ስለዚህም ይሁዳን በመውረር ቤተ መንግሥቱን ዘረፉ፤ ከኢዮራም መጨረሻ ልጅ ከአካዝያስ በቀር የንጉሡን ሚስቶችና ወንዶች ልጆች ሁሉ እስረኞች አድርገው ወሰዱአቸው።
18ከዚህም ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር ሊድን የማይችል ከባድ የአንጀት ሕመም በንጉሡ ላይ አመጣበት፤ 19ሕመሙም ለሁለት ዓመት ያኽል እየጸናበት ስለ ሄደ አንጀቱ ወጥቶ በብርቱ ሥቃይ ሞተ፤ በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ሕዝቡ ለቀድሞ አባቶቹ ይደረግ በነበረው ወግ ዐይነት ስለ ክብሩ እንጨት ከምረው እሳት አላነደዱለትም።
20ኢዮራም በሠላሳ ሁለት ዓመቱ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ስምንት ዓመት ገዛ፤ እርሱ በሞተ ጊዜ ማንም አላዘነለትም፤ በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ ይሁን እንጂ በነገሥታት መካነ መቃብር አልተቀበረም።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 21: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997