YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 26

26
ዳዊት እንደገና የሳኦልን ሕይወት ማትረፉ
1ጥቂት ሰዎች ከዚፍ ተነሥተው ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ በመምጣት “እነሆ፥ ዳዊት ከይሁዳ ምድረ በዳ ዳርቻ በተለይ ሐኪላ ተብሎ በሚጠራው ተራራ ላይ ተደብቆ ይገኛል” ብለው ነገሩት፤ #መዝ. 54። 2ሳኦልም በፍጥነት ተነሥቶ በእስራኤል ምርጥ የሆኑትን ሦስት ሺህ ወታደሮች በማስከተል ዳዊትን ለመፈለግ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ሄደ፤ 3ሳኦል በሐኪላ ተራራ ላይ በሚገኘው መንገድ አጠገብ በሔሲሞን ፊት ለፊት ሰፈረ፤ ዳዊትም በምድረ በዳ ነበር፤ ሳኦል እርሱን ለመፈለግ መምጣቱን ባየ ጊዜ፥ 4መልእክተኞች ልኮ በማሰለል ሳኦል በእርግጥ እዚያ መድረሱን ዐወቀ፤ 5ከዚያም በፍጥነት ተነሥቶ በመሄድ ሳኦልና የሠራዊቱ አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር የሚተኙበትን ቦታ አረጋገጠ፤ ሳኦል በሰፈሩ መካከል ተኝቶ ሳለ ወታደሮቹ በዙሪያው ይገኙ ነበር።
6ከዚህም በኋላ ዳዊት ሒታዊውን አቤሜሌክንና ከጸሩያ ልጆች የኢዮአብን ወንድም አቢሳን “ከእናንተ ከሁለታችሁ ከእኔ ጋር አብሮ ወደ ሳኦል ሰፈር የሚሄድ ማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
አቢሻይም “እኔ እሄዳለሁ” ሲል መለሰ።
7ስለዚህም በዚያው ምሽት ዳዊትና አቢሳን ወደ ሳኦል ሰፈር ገቡ፤ ሳኦልንም በሰፈሩ መካከል ተኝቶ አገኙት፤ ጦሩም በራስጌው በኩል መሬት ላይ ተተክሎ ነበር፤ አበኔርና ወታደሮቹም በዙሪያው ተኝተዋል፤ 8አቢሳም ዳዊትን “እግዚአብሔር በዛሬው ምሽት ጠላትህን በእጅህ ጥሎልሃል፤ ስለዚህ አሁን የገዛ ጦሩን አንሥቼ ልውጋውና ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ አንድ ምት ብቻ ስለሚበቃው ድጋሚ አያስፈልገውም!” አለው።
9ዳዊት ግን አቢሳን፦ “ልትገድለው አይገባህም! ቀብቶ ያነገሠውን ንጉሥ የሚጐዱ ሰዎችን እግዚአብሔር ራሱ ይቀጣል፤ 10በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ እግዚአብሔር ራሱ ሳኦልን ይገድለዋል፤ የሚሞትበት ጊዜ ደርሶ፥ አለበለዚያም በጦርነት መሞቱ አይቀርም፤ 11እግዚአብሔር ቀብቶ ባነገሠው ንጉሥ ላይ ጒዳት የማድረስ ተግባርስ ከእኔ ይራቅ! ይልቅስ ጦሩንና ውሃ መቅጃውን ይዘንበት እንሂድ” አለው። #1ሳሙ. 24፥6። 12ስለዚህም ዳዊት ጦሩንና ውሃ መቅጃውን ከሳኦል ራስጌ አንሥቶ እርሱና አቢሳ ከዚያ ሄዱ፤ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ከባድ እንቅልፍ ልኮባቸው ተጫጭኖአቸው ተኝተው ስለ ነበር ይህ ሁሉ ሲሆን ማንም ነቅቶ ያየና ያወቀ አልነበረም።
13ከዚህ በኋላ ዳዊት ከሸለቆው ባሻገር ወደሚገኘው ቦታ ተሻገረ፤ ከእነርሱም ራቅ ብሎ በተራራው ጫፍ ላይ ቆመ። 14ድምፁንም ከፍ አድርጎ ወደ ሳኦል ወታደሮችና ወደ አበኔር በመጮኽ “አበኔር ሆይ! መልስ ስጠኝ” አለው።
አበኔርም “እንዲህ እያልክ በንጉሡ ላይ የምትጮኽ አንተ ማነህ?” አለ።
15ዳዊትም “አበኔር! አንተ በእስራኤል የታወቅህ ታላቅ ሰው አይደለህምን? ታዲያ ጌታህን ንጉሡን በደንብ የማትጠብቀው ስለምንድን ነው? እነሆ፥ ከእኛ አንድ ሰው ጌታህን ለመግደል ወደ ሰፈር ገብቶ ነበር፤ 16ይህ የሠራኸው ሥራ ልክ አይደለም፤ አበኔር፥ እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፥ እግዚአብሔር ቀብቶ ያነገሠውን ጌታችሁን ንጉሡን መጠበቅ ስላልቻላችሁ ሁላችሁም ሞት ይገባችኋል! በራስጌው የነበረው የንጉሡ ጦርና እንዲሁም የውሃ መቅጃው አሁን የት እንዳለ እስቲ ተመልከት!” አለው።
17ሳኦልም የዳዊትን ድምፅ ለይቶ ስላወቀ “ዳዊት ልጄ ሆይ! በእርግጥ ይህ ቃል የአንተ ነውን?” ሲል ጠየቀ።
ዳዊትም “አዎ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! ድምፄ ነው ሲል መለሰ። 18ታዲያ፥ አንተ ጌታዬ እኔን አገልጋይህን ስለምን ታሳድደኛለህ? ያደረግኹት ነገር ምንድን ነው? ምንስ ወንጀል ፈጸምኩ? 19ንጉሥ ሆይ! የምልህን አድምጠኝ! አንተን በእኔ ላይ ያነሣሣህ እግዚአብሔር ቢሆን ኖሮ፥ መሥዋዕት በማቅረብ ቊጣውን እንዲመልስ ማድረግ በተቻለ ነበር፤ ነገር ግን ይህን ያደረጉት ሰዎች ከሆኑ ሄደህ ባዕዳን አማልክትን አምልክ ብለው እግዚአብሔር ከሰጠኝ ርስት ድርሻ ስላባረሩኝ በእግዚአብሔር ፊት የተረገሙ ይሁኑ። 20ከእግዚአብሔር ርቄ በባዕድ አገር እንድገደል አታድርግ፤ ይህን ያኽል ታላቅ የሆነ የእስራኤል ንጉሥ እንደ ቁንጫ የምቈጠረውን እኔን ስለምን ያሳድዳል? እንደ በረሓ ቆቅ የሚያድነኝስ ስለምንድን ነው?”
21ሳኦልም “በእርግጥ ተሳስቻለሁ፤ ልጄ ዳዊት ሆይ! ተመልሰህ ወደ እኔ ና፤ ዳግመኛ ልጐዳህ ከቶ አልፈልግም፤ በዛሬይቱ ሌሊት ሕይወቴን አትርፈሃል፤ እኔ እንደ ሞኝ ሆኜአለሁ! ከባድ የሆነ ስሕተትም ፈጽሜአለሁ!” ሲል መለሰ።
22ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ! እነሆ፥ ጦርህን ከወታደሮችህ አንድ ሰው መጥቶ ይውሰድ። 23ታማኞች ለሆኑ ለደጋግ ሰዎች የመልካም ሥራቸውን ዋጋ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፤ እነሆ፥ ዛሬ እግዚአብሔር አንተን በእጄ ጥሎልኝ ነበር፤ እኔ ግን እግዚአብሔር መርጦ ያነገሠህን አንተን ልጐዳ አልፈለግሁም። 24ዛሬ እኔ የአንተን ሕይወት እንዳከበርኩ፥ እግዚአብሔር እኔንም እንደዚሁ ከመከራ በማውጣት ይጠብቀኝ!”
25ሳኦልም ዳዊትን “ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ! ብዙ ነገርን ታደርጋለህ፤ ይሳካልሃልም” አለው።
ስለዚህም ዳዊት ወደ ፈለገበት ቦታ ሄደ፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ተመለሰ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in