YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25

25
የሳሙኤል መሞት
1ሳሙኤል ሞተ፤ መላው እስራኤላውያንም በአንድነት መጥተው አለቀሱለት፤ ከዚያም በኋላ በራማ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ቀበሩት።
ዳዊትና አቢጌል
ከዚያም በኋላ ዳዊት ወደ ፋራን ምድረ በዳ ሄደ፤ 2-3በዚያም ቤተሰቡ ከካሌብ ጐሣ የሆነ ናባል ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም የማዖን ተወላጅ ሲሆን በቀርሜሎስ ከተማ አጠገብ የእርሻ መሬት ነበረው፤ ታላቅ ባለጸጋ ከመሆኑም የተነሣ ሦስት ሺህ በጎችና አንድ ሺህ ፍየሎች ነበሩት፤ ሚስቱ አቢጌልም እጅግ የተዋበች አስተዋይ ሴት ስትሆን እርሱ ግን መልካም ጠባይ የጐደለው ባለጌ ሰው ነበር።
ናባል በቀርሜሎስ በጎቹን ያሸልት ነበር፤ 4ዳዊትም በበረሓ ሳለ ይህንኑ ወሬ ሰማ፤ 5ስለዚህም ዐሥር መልእክተኞችን መርጦ ወደ ቀርሜሎስ እንዲሄዱና ናባልን አግኝተው የእርሱን ሰላምታ እንዲያቀርቡለት አዘዛቸው፤ 6ለናባልም ይነግሩት ዘንድ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጣቸው፦ “ሰላም ላንተ፥ ሰላም ለቤትህ፥ ሰላም ያንተ ለሆነው ሁሉ ይሁን ብላችሁ ሰላምታ አቅርቡለት። 7በጎችህንም እንደምታሸልት ሰምቶአል፤ እረኞችህ ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜም ሁሉ ምንም ዐይነት ጒዳት እንዳላደረስንባቸው እንድታውቅ ይፈልጋል፤ በቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ ከመንጋቸው አንድ እንኳ አልተወሰደባቸውም፤ 8እነርሱንም ብትጠይቃቸው ይህንኑ ይነግሩሃል፤ እነሆ ዛሬ እኛ የደስታ ግብዣ በሚደረግበት ቀን መጥተናል፤ እኛንም በመልካም ሁኔታ ትቀበለን ዘንድ ዳዊት ጠይቆአል፤ ስለዚህ ለእኛ ለአገልጋዮችህና ለወዳጅህ ለዳዊት ስትል የሚቻልህን ስጦታ አድርግልን።”
9የዳዊት ሰዎችም ይህንኑ መልእክት በዳዊት ስም ለናባል አስረክበው ይጠባበቁ ጀመር፤ 10ናባልም በመጨረሻ “ኧረ ለመሆኑ ዳዊት ማን ነው? እኔ ስለ እርሱ ሰምቼም አላውቅም! እነሆ፥ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ከጌቶቻቸው በኰበለሉ አገልጋዮች ተሞልታለች! 11ስለዚህ እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም ለበጎች ሸላቾቼ ያረድኳቸውን እንስሶች አንሥቼ ከወዴት እንደ መጡ ለማላውቃቸው ሰዎች የምሰጥበት ምክንያት የለም!” አለ።
12መልእክተኞቹም ተመልሰው መጥተው ናባል ያለውን ሁሉ ለዳዊት ነገሩት፤ 13ዳዊትም “በሉ ሰይፋችሁን ታጠቁ!” የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም እንደ ታዘዙት አደረጉ፤ ዳዊትም ራሱ ሰይፉን ታጠቀ፤ ጓዝ የሚጠብቁ ሁለት መቶ ሰዎች ወደ ኋላ ትቶ አራት መቶ ሰዎች በማስከተል ገሥግሦ ለመሄድ ተነሣ። 14ከናባል አገልጋዮች አንዱም የናባልን ሚስት አቢጌልን እንዲህ አላት፤ “ዳዊት ካለበት በረሓ መልእክተኞችን ከሰላምታ ጋር ወደ ጌታችን ልኮ ነበር፤ እርሱ ግን በስድብ አዋረዳቸው፤ 15እነርሱ ግን ለእኛ በጎ አድራጊዎች ነበሩ፤ ምንም ችግር አልፈጠሩብንም፤ ከእነርሱ ጋር በዱር በነበርንበት ጊዜ ሁሉ ከእንስሶቻችን አንድ እንኳ ተሰርቆብን አያውቅም፤ 16መንጋዎቻችንን እየጠበቅን በቈየንበት ጊዜ ሁሉ በቀንም ሆነ በሌሊት እነርሱ ለእኛ አጥር ሆነውን ነበር። 17እባክሽን ይህን ጉዳይ አስቢበትና ማድረግ ስለሚገባሽ ነገር ወስኚ፤ አለበለዚያ ለጌታችንና ለቤተሰቡ ሁሉ አደገኛ ጥፋት ይሆናል፤ እርሱ እንደ ሆነ የማንንም ምክር የማይሰማ ደረቅ ሰው ነው!”
18አቢጌልም በፍጥነት ሁለት መቶ እንጀራ፥ ወይን ጠጅ የተሞላበት ሁለት የወይን አቁማዳ፥ አምስት የተጠበሱ በጎች፥ ዐሥራ ሰባት ኪሎ የተጠበሰ እሸት፥ አንድ መቶ ዘለላ ወይንና ሁለት መቶ የበለስ ፍሬ ጥፍጥፍ በአንድነት ሰብስባ በአህዮች ላይ ጫነች። 19ከዚህም በኋላ አገልጋዮቹን “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋላሁ” አለቻቸው፤ ለባልዋ ግን የነገረችው ቃል አልነበረም።
20እርስዋም በአህያ ላይ ተቀምጣ እየጋለበች በኮረብታው ጥግ በሚገኘው ጠመዝማዛ መንገድ ስትወርድ በድንገት ዳዊትና ተከታዮቹ ወደ እርስዋ ሲመጡ አገኘቻቸው፤ 21ዳዊትም በልቡ እንዲህ እያለ ያስብ ነበር፤ “የዚያን የማይረባ ሰው ሀብት በዚህ በረሓ ለምን ስጠብቅ ቈየሁ? የእርሱ ከሆነው ንብረት ምንም ነገር ተሰርቆበት አያውቅም፤ ታዲያ እኔ ስላደረግሁለት መልካም ነገር እርሱ የሚከፍለኝ ወሮታ ይህ ሆኖ ቀረ! 22ከመንጋቱ በፊት የእርሱ የሆኑትን ወንዶች ሁሉ አንድ እንኳ ሳላስቀር በሙሉ ሳልገድል ብቀር እግዚአብሔር እኔን በሞት ይቅጣኝ!”
23አቢጌልም ዳዊትን ባየችው ጊዜ በፍጥነት ከአህያዋ ወርዳ በዳዊት ጫማ አጠገብ መሬት ላይ ለጥ ብላ እጅ ነሣች፤ 24በጫማውም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ! እባክህ የእኔን የአገልጋይህን ቃል አድምጠኝ! በደሉን እኔ ልሸከም፤ 25የናባልን ጉዳይ ከቁም ነገር አታግባው! እርሱ ልክ እንድ አስሙ አጠራር ሞኝ ነው! ጌታዬ፥ የአንተ አገልጋዮች በመጡ ጊዜ እኔ በዚያ አልነበርኩም፤ #25፥25 ናባል፦ በዕብራይስጥ ናባል ማለት ሞኝ ማለት ነው። 26የበቀል እርምጃ በመውሰድ ጠላቶችህን እንዳትገድል የጠበቀህ ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ እነሆ፥ እኔ አሁን በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ ጠላቶችህና አንተን ለመጒዳት የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ቅጣታቸውን ይቀበሉ፤ 27ጌታዬ ሆይ! እባክህ ይህ እኔ አገልጋይህ ያመጣሁልህን ስጦታ ተቀብለህ ለአገልጋዮችህ ይሁን። 28ጌታዬ፥ አንተ የእግዚአብሔርን ጦርነት እየተዋጋህ ነው፤ በምትኖርበትም ዘመን ሁሉ ምንም ዐይነት ክፉ ነገር ማድረግን ስለማትፈልግ ስለ ፈጸምኩት በደል እባክህ ይቅር በለኝ፤ እግዚአብሔር አንተንና ዘሮችህን ለዘለዓለም ያነግሣል፤ 29ማንም ሰው በአንተ ላይ አደጋ ጥሎ ሊገድልህ ቢፈልግ አንድ ሰው ውድ የሆነ ሀብቱን እንደሚጠብቅ አምላክህ እግዚአብሔር አንተን በሰላም ይጠብቅሃል፤ ስለ ጠላቶችህም የሆነ እንደ ሆነ አንድ ሰው ድንጋዩን ከወንጭፍ እንደሚያስፈነጥር እግዚአብሔር ራሱ አሽቀንጥሮ ይጥላቸዋል። 30እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት፥ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ባደረገልህና በእስራኤልም ላይ በሚያነግሥህ ጊዜ፥ 31ምንም ዐይነት ጸጸት ወይም የኅሊና ወቀሳ አይደርስብህም። ጌታዬ ሆይ፥ ያለ ምክንያት ወይም የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ብለህ የገደልከው ሰው የለም፤ ስለዚህ ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር በሚባርክህ ጊዜ እኔንም አትርሳኝ።”
32ዳዊትም እንዲህ አላት፤ “ከእኔ ጋር እንድትገናኚ አንቺን ወደ እኔ የላከ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! 33በዛሬው ቀን ደም ከማፍሰስና በቀልንም ከመበቀል የጠበቀኝ መልካም አስተሳሰብሽ የተባረከ ይሁን፤ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። 34በአንቺ ላይ ጒዳት ከማድረስ እግዚአብሔር ጠብቆኛል፤ ፈጥነሽ ወደ እኔ ባትመጪ ኖሮ ግን፥ ከናባል ወንዶች አንድ እንኳ ሳላስተርፍ ከንጋት በፊት ሁሉንም ለመግደል በሕያው እግዚአብሔር ስም ምዬ ነበር።” 35ከዚያም በኋላ ዳዊት ያመጣችለትን ስጦታ ተቀብሎ “ወደ ቤትሽ በሰላም ተመልሰሽ ሂጂ፤ ልመናሽን ሰምቼአለሁ፤ የጠየቅሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አላት።
36አቢጌልም እንደ ቤተ መንግሥት ግብር ታላቅ ግብዣ በማድረግ ላይ ወደነበረው ወደ ናባል ተመልሳ ሄደች፤ እርሱም ሰክሮ በደስታ ይፈነድቅ ስለ ነበር እስከ ማግስቱ ጧት ድረስ ምንም ቃል አልነገረችውም፤ 37በማግስቱም ስካሩ ከበረደለት በኋላ ሁሉንም ነገር አስረዳችው፤ ልቡም በድንጋጤ ስለ ተመታ እንደ ድንጋይ ሆነ። 38ከዐሥር ቀኖች በኋላም እግዚአብሔር ስለ ቀሠፈው ናባል ሞተ።
39ዳዊትም የናባልን መሞት በሰማ ጊዜ “እኔን በመስደቡ እግዚአብሔር ናባልን ስለ ተበቀለውና እኔንም ከስሕተት ስለ ጠበቀኝ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እርሱ ናባልን ስለ ክፉ ሥራው ቀጥቶታል” አለ።
ከዚህም በኋላ ዳዊት ወደ አቢጌል መልእክተኛ ልኮ ሊያገባት መፈለጉን ገለጠላት። 40አገልጋዮቹም እርስዋ ወዳለችበት ወደ ቀርሜሎስ ሄደው “ሊያገባሽ ስለ ፈቀደ ወደ ዳዊት ልንወስድሽ መጥተናል” አሉአት።
41አቢጌልም ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ በመንሣት “እኔ ለእርሱ ገረዱ ነኝ፤ የአገልጋዮቹንም እግር ለማጠብ ዝግጁ ነኝ” አለች። 42ፈጥናም ተነሥታ በአህያዋ ላይ ተቀመጠች፤ በአምስት ገረዶችዋም ታጅባ ከዳዊት አገልጋዮች ጋር በመሄድ ሚስቱ ሆነች።
43ዳዊት ከዚህ በፊት የኢይዝራኤል ተወላጅ የሆነችውን አሒኖዓምን አግብቶ ነበር፤ አሁን ደግሞ አቢጌልን አገባ፤ 44ይህ በዚህ እንዳለ ሳኦል የዳዊት ሚስት የነበረችውን ልጁን ሜልኮልን የጋሊም ተወላጅ ለሆነው ለላዊሽ ልጅ ለፓልጢ ዳረለት። #2ሳሙ. 3፥14-26።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in