YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 3

3
ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብ ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔርን መለመኑ
(2ዜ.መ. 1፥3-12)
1ሰሎሞን የግብጽን ንጉሥ ሴት ልጅ በማግባት ከንጉሡ ጋር ወዳጅነት መሠረተ፤ እርስዋንም አምጥቶ ቤተ መንግሥቱን፥ ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ ዙሪያ ቅጽር ሠርቶ እስኪጨርስ ድረስ በዳዊት ከተማ አኖራት። 2በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደሱ ገና አልተሠራም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ በየኮረብታው መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። 3ሰሎሞን እግዚአብሔርን ይወድ ነበር፤ የአባቱንም የዳዊትን መመሪያ ይጠብቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ እንስሶችን እያረደ በተለያዩ ኰረብቶች ላይ መሥዋዕት ያቀርብ፥ ዕጣንም ያጥን ነበር።
4ታላቅ መሠዊያ የሚገኘው በገባዖን ስለ ነበር አንድ ቀን ሰሎሞን መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ፤ ከዚህም በፊት በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦአል፤ 5በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን በሕልም ተገለጠለትና “ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?” አለው።
6ሰሎሞንም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አገልጋይህ የነበረው አባቴ ዳዊት ደግ፥ ታማኝና ቅን ሰው በመሆኑ ጽኑ ፍቅርህን ስታሳየው ኖረሃል፤ ዛሬም በእርሱ እግር ተተክቶ በዙፋኑ የሚቀመጥ ልጅ በመስጠት ታላቅና ጽኑ የሆነውን የማያቋርጥ ፍቅርህን ገልጠህለታል፥ 7እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እነሆ እኔ በዕድሜ አነስተኛ ነኝ፤ የአመራር ልምድም የለኝም፤ አንተ ግን በአባቴ እግር ተተክቼ እንድነግሥ ፈቃድህ ሆኖአል፤ 8እነሆ እኔ የአንተ እንዲሆን በመረጥከውና ከብዛቱ የተነሣ ሊቈጠር በማይችል ሕዝብ መካከል እገኛለሁ፤ 9ስለዚህ ክፉውንና በጎውን በመለየት ሕዝብህን በትክክለኛ ፍርድ ለመምራት የሚያስችለኝን ጥበብ ስጠኝ፤ ይህ ካልሆነ ግን ታላቅ ሕዝብህን እንዴት ልመራ እችላለሁ?”
10ሰሎሞን ይህን በመጠየቁ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው፤ 11እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ለራስህ ረጅም ዕድሜ ወይም ሀብት ለማግኘት ወይም ጠላቶችህ እንዲጠፉልህ መመኘት ሳይሆን በትክክለኛ ፍርድ ማስተዳደር የምትችልበትን ጥበብ ስለ ጠየቅህ፥ 12እነሆ የጠየቅኸውን አደርጋለሁ፤ እንዲያውም ማንም ሰው ከዚህ በፊት ካገኘውና ወደ ፊትም ሊያገኘው ከሚችለው የሚበልጥ ጥበብንና አስተዋይነትን እሰጥሃለሁ፤ 13ከዚህም በላይ አንተ ያልጠየቅከውንም ሁሉ ጨምሬ እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም በዘመንህ ማንኛውም ሌላ ንጉሥ ያላገኘውን ብልጽግናና ክብር አበዛልሃለሁ። 14አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ብትሄድና ለእኔ ብትታዘዝ፥ ሕጌንና ትእዛዞቼንም ብትፈጽም ረጅም ዕድሜ እሰጥሃለሁ።”
15ሰሎሞን ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እግዚአብሔር በሕልም ተገልጦ ያነጋገረው መሆኑን ተገነዘበ፤ ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆሞ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ከዚህም በኋላ ባለሟሎቹ ለሆኑ ባለሥልጣኖች ሁሉ ግብዣ አደረገ።
ጥበብ የሞላበት የሰሎሞን ፍትሕ
16አንድ ቀን ሁለት ጋለሞታዎች መጥተው በሰሎሞን ፊት ቀረቡ፤ 17ከእነርሱም አንደኛይቱ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ሆይ! ይህች ሴትና እኔ በአንድ ቤት አብረን ስንኖር በዚያው በምንኖርበት ቤት ወንድ ልጅ ወለድኩ፤ 18እኔ በወለድኩ በሦስተኛው ቀን እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደች፤ በዚያ ቤት ውስጥ ከሁለታችን በቀር ሌላ ማንም አልነበረም። 19ከዕለታት አንድ ቀን ሌሊት በላዩ ላይ ተኝታበት ስለ ታፈነ ልጁ ሞተ፤ 20እኔ ተኝቼ ሳለሁ ሌሊት ተነሥታ ታቅፌው የተኛሁትን ልጄን ወስዳ በእርስዋ አልጋ ላይ ካስተኛች በኋላ የሞተውን ልጅዋን አምጥታ በእኔ አልጋ ላይ በጐኔ አስተኛችው። 21በማግስቱ ማለዳ ተነሥቼ ልጄን ለማጥባት ስዘጋጅ የሞተ ሆኖ አገኘሁት፤ ትኲር ብዬ ስመለከተው እኔ የወለድኩት ልጅ አለመሆኑን ተገነዘብኩ።”
22ሁለተኛይቱ ሴት ግን፥ “አይደለም! በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፤ የሞተው ግን የአንቺ ነው!” አለች።
የመጀመሪያይቱ ሴት “አይደለም! የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ በሕይወት ያለው ግን የእኔ ልጅ ነው!” አለች።
በዚህም ዐይነት በንጉሡ ፊት ተከራከሩ።
23ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን “አንደኛዋ ‘በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፤ የሞተው ግን የአንቺ ነው!’ ትላለች፤ ሌላይቱ ደግሞ ‘አይደለም! የአንቺ ልጅ ሞቶአል፤ የእኔ ልጅ በሕይወት ያለው ነው!’ ትላታለች አለ።” 24ንጉሡም ሰይፍ እንዲያመጡለት አዘዘ፤ ሰይፍም አመጡለት፤ 25“በሉ እንግዲህ በሕይወት ያለውን ልጅ ለሁለት ቊረጡና ለእያንዳንዷ ሴት ግማሽ አካሉን ስጡ” ሲል አዘዘ።
26እውነተኛይቱ እናት ግን ለልጅዋ በመራራት አዝና፥ “ንጉሥ ሆይ! እባክህ ልጁን አትግደለው! ለእርስዋ ይሰጣት!” አለች።
ሌላይቱ ሴት ግን “ለእኔም ለእርስዋም አይሁን! ለሁለት ይቈረጥ!” አለች።
27ከዚህ በኋላ ሰሎሞን “ሕፃኑን አትግደሉት! እውነተኛይቱ እናት እርስዋ ስለ ሆነች ለመጀመሪያይቱ ሴት ስጡአት!” ሲል አዘዘ።
28እስራኤላውያን ይህን የፍርድ ውሳኔ በሰሙ ጊዜ ሰሎሞን የሕዝብ ጉዳዮችን በትክክለኛ ፍርድ የሚወስንበትን ጥበብ እግዚአብሔር የሰጠው መሆኑን ስለ ተገነዘቡ ታላቅ አክብሮት ሰጡት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in