YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 20

20
የሰማርያ በሶርያ ጦር መከበብ
1የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ መላ ሠራዊቱን በአንድነት ሰበሰበ፤ ብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች ባሉአቸው ሠላሳ ሁለት ነገሥታት ተደግፎ በመዝመት የእስራኤል ዋና ከተማ የሆነችውን ሰማርያን ከቦ አደጋ ጣለባት። 2ከዚህም በኋላ ንጉሥ ቤንሀዳድ በከተማይቱ ወደሚገኘው ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ፥ “ቤንሀዳድ እንዲህ ይላል ብሎ መልእክተኞችን ላከ፦ 3‘ብርህና ወርቅህ፥ ውብ የሆኑት ሚስቶችህና ጠንካሮች የሆኑ ልጆችህ የእኔ ናቸው።’ ”
4አክዓብም “ለጌታዬ ለንጉሥ ቤንሀዳድ አንተ ባልከው እስማማለሁ፤ እኔና የእኔ የሆነ ሁሉ የአንተ ነው።” አለ።
5ከጥቂት ጊዜም በኋላ እነዚያው መልእክተኞች ከንጉሥ ቤንሀዳድ ሌላ ትእዛዝ ይዘው እንደገና ወደ አክዓብ መጡ፤ ትእዛዙም እንዲህ የሚል ነበር፤ “ብርህንና ወርቅህን፥ ሚስቶችህንና ልጆችህን እንድታስረክበኝ መልእክት ልኬብህ እንደ ነበር ይታወሳል፤ 6አሁን ደግሞ ቤተ መንግሥትህንና የባለሥልጣኖችህን ቤት ሁሉ በርብረው ዋጋ ያለውን ንብረት ሁሉ ይዘው እንዲመጡ የጦር መኰንኖቼን እልካለሁ፤ እነርሱም ነገ ጧት በዚሁ ሰዓት እዚያ ይደርሳሉ።”
7ንጉሥ አክዓብም የሀገሪቱን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ “ይህ ሰው ምን ዐይነት ጠብ እንደሚፈልግ ተመልከቱ። ከዚህ በፊት ሚስቶቼንና ልጆቼን፥ ብሬንና ወርቄን እንዳስረክበው ጠይቆኝ ተስማምቼ ነበር” አላቸው።
8ሽማግሌዎቹና ሕዝቡም “እርሱ ለሚልህ ነገር ሁሉ ግምት አትስጠው፤ እሺም አትበለው” አሉት።
9ስለዚህም አክዓብ ለቤንሀዳድ መልእክተኞች “ለጌታዬ ለንጉሡ፥ ‘ከዚህ በፊት ባቀረብክልኝ ጥያቄ ተስማምቼ ነበር፤ አሁን ባቀረብክልኝ በሁለተኛው ጥያቄ ግን ልስማማበት አልችልም ብሎአል’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው።
መልእክተኞቹም ተመልሰው በመሄድ መልሱን ነገሩት፤ 10ቤንሀዳድም “በሰማርያ ለያንዳንዱ ወታደር አንዳንድ ጭብጥ ዐፈር ሊዳረስ እስከማይችል ድረስ ብዙ ወታደሮችን ባላሰልፍ አማልክት ይቅሠፉኝ!” ብሎ የዛቻ መልእክቱን መልሶ ላከበት።
11ንጉሥ አክዓብ መልእክተኞቹን “ ‘እውነተኛ ወታደር መደንፋት የሚገባው ከጦርነት ድል በኋላ እንጂ ከጦርነት በፊት አይደለም’ ብላችሁ ለንጉሥ ቤንሀዳድ ንገሩት” ሲል መለሰላቸው።
12ቤንሀዳድና የእርሱ የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞቹ የሆኑ ሌሎችም ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው ሲጠጡ ሳሉ የአክዓብ መልእክት ደረሰ፤ በዚህን ጊዜ ቤንሀዳድ በከተማይቱ ላይ አደጋ ለመጣል እንዲዘጋጁ ትእዛዝ ሰጠ፤ ስለዚህም እነርሱ ፈጥነው በመንቀሳቀስ ቦታ ቦታቸውን ያዙ።
13በዚህን ጊዜ አንድ ነቢይ ወደ ንጉሥ አክዓብ ቀርቦ “እግዚአብሔር ‘ከቤንሀዳድ ሠራዊት ብዛት የተነሣ አትፍራ! እኔ ዛሬ በዚህ ሠራዊት ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አደርጋለሁ፤ አንተም ደግሞ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ይልሃል” አለው።
14አክዓብም “ግንባር ቀደም ሆኖ የሚዘምተው ማን ይሁን?” ሲል ጠየቀ።
ነቢዩም “እግዚአብሔር ‘በአውራጃ አስተዳዳሪዎች የሚታዘዙ ወጣትነት ያላቸው ወታደሮች ግንባር ቀደም ሆነው ይዝመቱ’ ይላል” አለው፤
ንጉሡም “ጦርነቱን ማ ይጀምር” ሲል ጠየቀ።
ነቢዩም “አንተ ራስህ ጀምር” አለው።
15ስለዚህ ንጉሡ ብዛታቸው ሁለት መቶ ሠላሳ ሁለት ብቻ የሆነ በአውራጃ አስተዳዳሪዎች ትእዛዝ ሥር የሆኑትን ወጣትነት ያላቸውን ወታደሮች ጠራ፤ ቀጥሎም ጠቅላላ ብዛቱ ሰባት ሺህ የሆነ የእስራኤልን ሠራዊት ጠራ።
16ቤንሀዳድና የእርሱ የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞች የሆኑ ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ በመጠጥ ሰክረው በነበሩበት ጊዜ እኩለ ቀን ላይ የእስራኤል ሠራዊት ወጣ፤ 17ወጣቶቹም ወታደሮች ግንባር ቀደም ሆነው ወደ ፊት አመሩ፤ ቤንሀዳድ ልኮአቸው የነበሩትም ቃፊሮች “አንድ የወታደሮች ቡድን ከሰማርያ ወጥቶ ወደዚህ እየመጣ ነው” ብለው ነገሩት። 18ቤንሀዳድም “ቃፊሮቹ አመጣጣቸው ለጦርነትም ይሁን ለሰላም፥ ከነሕይወታቸው ይዛችሁ አምጡልኝ” ሲል አዘዘ።
19በእስራኤል ሠራዊት ደጀንነት ወጣቶቹ ወታደሮች ግንባር ቀደም ሆነው ወጡ፤ 20እያንዳንዱም ውጊያ የገጠመውን ጠላቱን ገደለ፤ ሶርያውያን ሸሹ፤ እስራኤላውያንም ያሳድዱአቸው ጀመር፤ ቤንሀዳድ ግን በፈረሱ ላይ በመቀመጥ ከጥቂት ፈረሰኞች ጋር ሸሽቶ አመለጠ፤ 21ንጉሥ አክዓብም ወደ ጦሩ ሜዳ ገብቶ የጠላትን ፈረሶችና ሠረገሎች ማረከ፤ በሶርያውያንም ላይ ታላቅ ጥፋት በማድረስ ድል አደረጋቸው።
22ከዚህ በኋላ ነቢዩ ወደ ንጉሥ አክዓብ ቀርቦ የሶርያ ንጉሥ በሚመጣው የጸደይ ወራት እንደገና አደጋ ስለሚጥልብህ “ተመልሰህ ሂድና ሠራዊትህን በማጠናከር አደራጅ፤ ጥንቃቄ የሞላበትንም የጦርነት ስልት አዘጋጅ” አለው።
ሶርያውያን እንደገና አደጋ መጣላቸው
23ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖች ንጉሥ ቤንሀዳድን እንዲህ አሉት፤ “የእስራኤል አማልክት የተራራ አማልክት ናቸው፤ እስራኤላውያን እኛን ማሸነፍ የቻሉት ስለዚህ ነው፤ በሜዳማ ስፍራዎች ጦርነት ብንገጥማቸው ግን እናሸንፋለን፤ 24ስለዚህ አሁን ሠላሳ ሁለቱን ነገሥታት ከጦር አዛዥነታቸው ሽረህ፥ በእነርሱ ቦታ ሌሎችን የጦር አዛዦች ሹም፤ 25ከዚህ በፊት የተደመሰሰውን የሚያኽል ብዙ ሠራዊትና እንዲሁም በቀድሞዎቹ ልክ ፈረሶችንና ሠረገሎችን አደራጅ፤ ከዚያም በኋላ እስራኤላውያንን በሜዳ ተዋግተን ድል እንነሣቸዋለን።”
ንጉሥ ቤንሀዳድም በእነርሱ ምክር ተስማምቶ ለመፈጸም ወሰነ፤ 26ስለዚህም በተከታዩ የጸደይ ወቅት ሠራዊቱን በአንድነት ጠርቶ በእስራኤል ላይ አደጋ ለመጣል ወደ አፌቅ ከተማ ገሠገሠ፤ 27እስራኤላውያንም ተጠርተው ከሚያስፈልጋቸው ስንቅና ትጥቅ ጋር ለጦርነት ተዘጋጁ፤ እነርሱም ወደ ጦርነቱ በመዝመት በሁለት ቡድን ተከፍለው ከሶርያውያን ፊት ለፊት ባለው ቦታ ሰፈሩ፤ የእስራኤል ወታደሮች ቊጥር አገሩን ካጥለቀለቀው ከሶርያውያን ሠራዊት ብዛት ጋር ሲነጻጸር ከሁለት የተከፈሉ የጥቂት ፍየሎች መንጋዎች ይመስሉ ነበር።
28አንድ የእግዚአብሔር ነቢይ ወደ ንጉሥ አክዓብ ቀርቦ “እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ ‘ሶርያውያን፦ እግዚአብሔር የኮረብቶች አምላክ እንጂ የሜዳዎች አምላክ አይደለም ብለዋል፤ ከዚህም የተነሣ እኔ እጅግ ብዙ በሆነው ሠራዊታቸው ላይ ድልን አቀዳጅሃለሁ፤ አንተና ሕዝብህም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ’ ” አለው።
29ሶርያውያንና እስራኤላውያን ፊት ለፊት ተፋጠው በየጦር ሰፈራቸው እስከ ሰባት ቀን ቈዩ፤ በሰባተኛውም ቀን ጦርነት ጀምረው በዚያኑ ቀን እስራኤላውያን አንድ መቶ ሺህ የሶርያውያንን እግረኛ ጦር ወታደሮችን ገደሉ። 30ከሞት የተረፉትም ሶርያውያን ሸሽተው ወደ አፌቅ ከተማ ገቡ፤ በዚያም ቊጥራቸው ኻያ ሰባት ሺህ በሚሆኑት ወታደሮች ላይ የከተማው ቅጽር ተንዶባቸው አለቁ።
ቤንሀዳድም አምልጦ ወደ ከተማይቱ በመግባት ከአንድ ቤት በስተ ኋላ በኩል ባለው ክፍል ውስጥ ተደበቀ። 31ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖችም ወደ እርሱ ቀርበው “የእስራኤል ነገሥታት ምሕረት አድራጊዎች መሆናቸውን ሰምተናል፤ ስለዚህ በወገባችን ማቅ ታጥቀን፥ በራሳችንም ገመድ ጠምጥመን ወደ እስራኤል ንጉሥ ዘንድ ሄደን ምሕረት እንድንጠይቀው ፍቀድልን፤ ምናልባትም ሕይወትህን ያተርፍ ይሆናል” አሉት። 32ከዚህም በኋላ እነርሱ በወገባቸው ማቅ ታጥቀው፥ በራሳቸውም ገመድ ጠምጥመው ወደ ንጉሥ አክዓብ በመሄድ “አገልጋይህ ቤንሀዳድ ምሕረት አድርገህ ሕይወቱን እንድታተርፍለት ይማጠንሃል” አሉት።
አክዓብም “እርሱ እስከ አሁን በሕይወት አለ ማለት ነውን? ከሆነስ መልካም ነው፤ እንግዲህ እርሱ ለእኔ እንደ ወንድም ነው!” ሲል መለሰላቸው።
33የንጉሥ ቤንሀዳድ ባለሟሎች የምሕረት መልእክት ይጠባበቁ ስለ ነበር፥ አክዓብ “ወንድሜ” ሲል በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ቀበል አድርገው “አንተ እንዳልከው ቤንሀዳድ በእርግጥ ወንድምህ ነው!” አሉት።
አክዓብም “ወደ እኔ አምጡት!” አላቸው። ቤንሀዳድም በመጣ ጊዜ፥ አክዓብ ወደ ሠረገላው ገብቶ እንዲቀመጥ ቤንሀዳድን ጋበዘው። 34ቤንሀዳድም አክዓብን “አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልስልሃለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ አንተም በደማስቆ ለራስህ የንግድ ማእከል ልታቋቊም ትችላለህ” አለው።
አክዓብም “እንግዲያውስ በዚህ ስምምነት መሠረት እኔም በነጻ እለቅሃለሁ” ሲል መለሰለት።
አክዓብም በዚህ ዐይነት ከእርሱ ጋር የውል ስምምነት አድርጎ በነጻ እንዲሄድ ፈቀደለት።
አንድ ነቢይ በአክዓብ ላይ ወደፊት የሚደርስበትን ፍርድ መናገሩ
35የነቢያት ወገን የሆነ አንድ ነቢይ በእግዚአብሔር ታዞ የእርሱ ጓደኛ የሆነውን ሌላ ነቢይ “ምታኝ!” አለው። ነቢዩ ግን እርሱን ለመምታት አልፈቀደም፤ 36ስለዚህም ያ ነቢይ “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም እምቢ ስላልክ፥ ከእኔ ተለይተህ እንደ ሄድክ ወዲያውኑ አንድ አንበሳ ይገድልሃል” አለው፤ በእርግጥም ከእርሱ ተለይቶ እንደ ሄደ አንበሳ በድንገት ወደ እርሱ መጥቶ ገደለው። #1ነገ. 13፥24።
37ከዚህም በኋላ ነቢዩ ወደ ሌላ ሰው ሄዶ “ምታኝ!” አለው፤ ያም ሰው “እሺ” በማለት በኀይል ደብድቦ አቈሰለው፤ 38ነቢዩ ማንነቱ እንዳይታወቅ ፊቱን በጨርቅ ሸፈነ፤ ሄዶም በዚያ በኩል የሚያልፈውን የእስራኤልን ንጉሥ ለመጠበቅ በመንገድ ዳር ቆመ። 39ንጉሡም በአጠገቡ ሲያልፍ፥ ነቢዩ ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ! እኔ በጦርነት ውስጥ በውጊያ ላይ ነበርኩ፤ በዚያን ጊዜም ከወታደሮቹ አንዱ ከጠላት ወገን አንድን ሰው ማርኮ በማምጣት ‘ይህን ሰው ጠብቅ፤ ቢያመልጥ ግን በእርሱ ፈንታ አንተ ትገደላለህ ወይም ሠላሳ አራት ኪሎ የሚመዝን ጥሬ ብር መቀጫ ትከፍላለህ’ አለኝ። 40ነገር ግን እኔ ሥራ በዝቶብኝ ወዲያና ወዲህ ስል ሰውየው አምልጦ ሄደ።”
ንጉሡም “በራስህ ላይ ስለ ፈረድህ መቀጣት ይገባሃል” አለው።
41ነቢዩ ፊቱ የተሸፈነበትን ጨርቅ ፈጥኖ አወለቀ፤ ንጉሡም ይህ ሰው ከነቢያት ወገን አንዱ መሆኑን ወዲያውኑ ዐወቀ። 42ከዚህ በኋላ ያ ነቢይ ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ ‘እኔ ይገደል’ ብዬ የፈረድኩበትን ሰው እንዲያመልጥ ስለ ፈቀድህ በእርሱ ፈንታ አንተ በሞት ትቀጣለህ፤ የዚያ ሰው ሠራዊት አምልጦ እንዲሄድ ስላደረገ ሠራዊትህም ይደመሰሳል፤ ”
43ንጉሡም በማዘንና በመበሳጨት በሰማርያ ወደሚገኘው ቤተ መንግሥቱ ተመልሶ ሄደ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in