YouVersion Logo
Search Icon

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 2

2
ዳዊት ለሰሎሞን የሰጠው የመጨረሻ መመሪያ
1ዳዊት የሚሞትበት ወቅት በተቃረበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን ጠርቶ ይህን የመጨረሻ ትእዛዝ ሰጠው፤ 2“እነሆ እኔ ሰው ሁሉ እንደሚሞት የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ እንግዲህ በርታ! ቈራጥ ሰው ሁን፤ 3አምላክህ እግዚአብሔር እንድታደርግ የሚያዝህን ሁሉ አድርግ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ የምታደርገው ማናቸውም ነገር እንዲከናወንልህ በሙሴ አማካይነት በተሰጠው ሕግ የተጻፉትን የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ፥ ሥርዓትና ፈቃድ ሁሉ ጠብቅ፤ 4በዚህ ሁሉ ነገር ታዛዥ ብትሆንለት፥ ‘ዘሮችህ በጥንቃቄ ተጠብቀው ቢኖሩ፥ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በፊቴ በቅንነት ቢመላለሱ፥ በእስራኤል ዙፋን ላይ ነግሦ የሚገዛ ዘር አላሳጣህም’ ብሎ የነገረኝን የተስፋ ቃል ይፈጽማል።
5“የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የእስራኤል ሕዝብ የጦር መሪዎች ከነበሩት በኔር ልጅ አበኔርና በይቴር ልጅ ዐማሣ ላይ ያደረገውን ታስታውሳለህ፤ ሁለት በጦርነት ጊዜ ላፈሰሱት ደም በቀል በሰላም ጊዜ እነርሱን ገድሎ የወገቡን ድግና የእግሩን ጫማ በደም በክሎ በእኔ ላይ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ። #2ሳሙ. 3፥27፤ 20፥10። 6እንግዲህ ባለህ ጥበብ፥ ሊፈጸም የሚገባውን ነገር አድርግ፤ ዕድሜ ጠግቦ በሰላም እንዲሞት አትፍቀድለት።
7“ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ የቸርነት ሥራ ስላደረጉልኝ ለገለዓዳዊው ለባርዚላይ ልጆች ግን መልካም ነገር በማድረግ ተንከባከባቸው፤ በማዕድህም ከሚመገቡት መካከል ይሁኑ። #2ሳሙ. 17፥27-29።
8“ከዚህም ጋር መረሳት የሌለበት የብንያም ክፍል በሆነችው በባሑሪም ከተማ ውስጥ የሚኖረው የጌራ ልጅ ሺምዒ አለ፤ እርሱ ወደ ማሕናይም በሄድኩበት ቀን በእኔ ላይ የስድብ ውርጅብኝ አውርዶብኛል፤ ይሁን እንጂ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ባገኘኝ ጊዜ እንደማላስገድለው በእግዚአብሔር ስም ቃል ገብቼለት ነበር፤ #2ሳሙ. 16፥5-13፤ 19፥16-23። 9አንተ ግን እርሱንም ከቅጣት ነጻ አታድርገው፤ ባለህ ጥበብ ምን መደረግ እንዳለበት አንተ ራስህ ታውቃለህ፤ በሞት የሚቀጣ መሆኑንም አትዘንጋ።”
የዳዊት መሞት
10ዳዊት ሞተ፤ የእርሱ ከተማ በሆነችው በኢየሩሳሌምም ተቀበረ፤ 11ዳዊት በኬብሮን ሰባት ዓመት፥ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት በድምሩ አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ነገሠ። #2ሳሙ. 5፥4-5፤ 1ዜ.መ. 3፥4። 12ሰሎሞንም በአባቱ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ የመንግሥቱም ሥልጣን እጅግ የጸና ሆነ። #1ዜ.መ. 29፥23።
የአዶንያስ መሞት
13የሐጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም “ወደ እኔ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው።
እርሱም “አዎን በሰላም ነው የመጣሁት” ሲል መለሰ። 14ቀጠል አድርጎም “እኔ የምጠይቅሽ ጉዳይ አለኝ” አላት።
እርስዋም “ጉዳይህ ምንድን ነው?” አለችው።
15አዶንያስም እንዲህ አላት፦ “ንጉሥ መሆን የሚገባኝ እኔ እንደ ነበርኩና ይህንንም በእስራኤል ምድር የሚኖር ሁሉ በተስፋ ይጠባበቅ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከእግዚአብሔር ስለ ተወሰነ ለእኔ መሰጠት የሚገባው መንግሥት ተላልፎ ለወንድሜ ሆኖአል። 16አሁንም የምጠይቅሽ አንድ ጉዳይ ስላለኝ እምቢ በማለት አታሳፍሪኝ።”
ቤርሳቤህም “ጉዳይህ ምንድን ነው?” ስትል ጠየቀችው።
17እርሱም “ንጉሥ ሰሎሞን አንቺን እምቢ እንደማይልሽ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ አቢሻግ ተብላ የምትጠራውን ሹኔማይት ልጃገረድ በሚስትነት እንዲድርልኝ እባክሽ አማልጅኝ” አላት። #1ነገ. 1፥3-4።
18እርስዋም “መልካም ነው! ይህን ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” አለችው።
19ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጉዳይ ልትነግር ወደ ንጉሡ ገባች፤ ንጉሡም ከተቀመጠበት ተነሥቶ እናቱን እጅ በመንሣት ተቀበላት፤ እርሱም በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ በኋላ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት፤ 20እርስዋም “እንድትፈጽምልኝ የምጠይቅህ አንድ ትንሽ ጉዳይ አለኝ፤ እባክህ እምቢ በማለት አታሳፍረኝ” አለችው።
ንጉሡም “እናቴ ሆይ! አላሳፍርሽም፤ ጉዳዩ ምንድን ነው” አላት።
21እርስዋም “ወንድምህ አዶንያስ አቢሻግን ሚስት አድርጎ ያገባ ዘንድ ፍቀድለት” አለችው።
22ንጉሡም “አቢሻግን በሚስትነት እንድድርለት ብቻ ለምን ትጠይቂኛለሽ? መንግሥቴንም ጭምር እንድለቅለት ለምን አልጠየቅሽኝም? እርሱ እኮ ታላቅ ወንድሜ ነው፤ ለምን ለካህኑ አብያታርና ለኢዮአብም ልዩ አስተያየት እንዳደርግላቸው አትጠይቂላቸውም!” አላት። 23ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ሲል ማለ፦ “አዶንያስ ይህን በማቀዱ በሕይወቱ እንዲከፈል ባላደርግ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ በበለጠም ይቅጣኝ! 24እግዚአብሔር በአባቴ በዳዊት ዙፋን ላይ አስቀምጦ መንግሥቴን የጸና አድርጎልኛል፤ ይህን መንግሥት ለእኔና ለዘሮቼ በመስጠት ቃሉን ጠብቆአል፤ እንግዲህ አዶንያስ በዚህ በዛሬው ቀን በሞት እንደሚቀጣ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ!”
25ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ አዶንያስን ገደለው።
የአብያታር መሳደድና የኢዮአብ በሞት መቀጣት
26ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ካህኑን አብያታርን እንዲህ አለው፤ “ወደ ትውልድ አገርህ ወደ ዐናቶት ሂድ፤ አንተ በሞት ልትቀጣ ይገባህ ነበር፤ ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ትሸከም ስለ ነበርክ ከእርሱም ጋር የመከራው ሁሉ ተካፋይ ስለ ነበርክ እኔ አሁን አልገድልህም #1ሳሙ. 22፥20-23፤ 2ሳሙ. 15፥24። 27ከዚህም በኋላ ሰሎሞን አብያታርን የእግዚአብሔር ካህን ሆኖ ከሚያገለግልበት የክህነት ሥልጣን ሽሮ አባረረው፤ በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር በሴሎ ስለ ካህኑ ዔሊና ስለ ትውልዱ የተናገረው ቃል ተፈጸመ።” #1ሳሙ. 2፥27-36።
28በአንድ በኩል የአዶንያስ ደጋፊ፥ በሌላ በኩል ደግሞ የአቤሴሎም ተቃዋሚ የሆነው ኢዮአብ ይህን የተፈጸመውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ስለዚህም ሸሽቶ ወደ ተቀደሰው ድንኳን ሄደ፤ በዚያም የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ተማጠነ፤ 29ኢዮአብ ወደ ተቀደሰ ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መገኘቱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፥ ኢዮአብን እንዲገድለው ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ። 30እርሱም ወደ ተቀደሰው ድንኳን ሄዶ ኢዮአብን “ከዚህ ድንኳን እንድትወጣ ንጉሡ አዞሃል” አለው።
ኢዮአብ ግን “አልወጣም! እዚሁ እሞታለሁ!” አለ።
በናያም ተመልሶ ኢዮአብ ያለውን ለንጉሡ ነገረው።
31ሰሎሞንም በናያን እንዲህ አለው፦ “ኢዮአብ እንዳለህ ግደለውና ቅበረው፤ በዚህ አኳኋን ኢዮአብ ካፈሰሰው ንጹሕ ደም በደል የእኔንና የአባቴን ቤት የነጻን አድርገን። 32አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ ስለ ገደላቸው ስለ እነዚያ ሰዎች ደም እግዚአብሔር ኢዮአብን ይቀጣዋል፤ ኢዮአብ ከእርሱ የተሻሉትን ሁለት ንጹሓን ሰዎች ገድሎአል፤ እነርሱም የእስራኤል ጦር አዛዥ አበኔርና የይሁዳ ጦር አዛዥ ዐማሣ ነበሩ። 33ኢዮአብ እነዚህን ሰዎች በመግደሉ በእርሱ ላይ የተፈጸመበት ቅጣት በእርሱና በዘሮቹ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር፤ በዙፋኑ ላይ ለሚቀመጡት ለዳዊት ዘሮች ግን የእግዚአብሔር ሰላም ለዘለዓለም አይለያቸው።”
34ስለዚህ በናያ በታዘዘው መሠረት ኢዮአብን ገደለው፤ በቤቱም አጠገብ በሚገኘው በረሓ ተቀበረ። 35ንጉሥ ሰሎሞን በኢዮአብ ፈንታ በናያን የሠራዊቱ አዛዥ፥ በአብያታርም ፈንታ ሳዶቅን ካህን አድርጎ ሾመ።
የሺምዒ መሞት
36ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ሽምዒን አስጠርቶ እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “በዚህ በኢየሩሳሌም የራስህን መኖሪያ ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ከዚያ ወደየትም አትሂድ፤ 37ከከተማይቱ ወጥተህ የቄድሮንን ወንዝ ተሻግረህ ብትገኝ በእርግጥ ትሞታለህ፤ ለደምህም ተጠያቂ ራስህ ነህ።”
38ሺምዒም “ንጉሥ ሆይ! ውሳኔህ ትክክል ነው፤ እኔ አገልጋይህ አንተ ጌታዬ እንዳልከው አደርጋለሁ” ሲል መለሰ፤ ስለዚህ በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ።
39ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ሁለቱ የሺምዒ አገልጋዮች የማዕካ ልጅ ወደ ሆነው አኪሽ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ጋት ንጉሥ ኰብልለው ሄዱ፤ ሺምዒም ባሪያዎቹ በጋት መኖራቸው ተነገረው፤ 40አህያውን ጭኖ እነርሱን ለማግኘት በጋት ወደሚኖረው ወደ ንጉሥ አኪሽ ሄደ፤ እነርሱንም በዚያ ስላገኛቸው ወደ ቤቱ መልሶ አመጣቸው። 41ሰሎሞን ሺምዒ ከኢየሩሳሌም ወደ ጋት ሄዶ መመለሱን ሰማ። 42ንጉሡም ሽምዒን አስጠርቶ “ከኢየሩሳሌም እንዳትወጣ በእግዚአብሔር ስም አስምዬህ አልነበረምን? ወጥተህ ብትገኝ ግን በእርግጥ እንደምትሞት አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚህስ ተስማምተህ ትእዛዜን እንደምትፈጽም ቃል ገብተህልኝ አልነበረምን?” አለው። 43“ታዲያ፥ በእግዚአብሔር ስም ከማልክ በኋላ የእግዚአብሔርን መሐላ ለምን አልጠበቅህም? ትእዛዜንስ ስለምን አላከበርክም? 44በአባቴ በንጉሥ ዳዊት ላይ የፈጸምከውን በደል ሁሉ በደንብ ታውቃለህ፤ አንተ ስላደረግኸው ክፉ ነገር እግዚአብሔር ራሱ ይቀጣሃል፤ 45እኔን ግን እግዚአብሔር ይባርከኛል፤ የዳዊት መንግሥትም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።”
46ከዚህም በኋላ ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ሺምዒን እንዲገድል ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ ሺምዒን ገደለው፤ በዚህም ዐይነት መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ የጸና ሆነ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in