1 የዮሐንስ መልእክት 4
4
እውነተኛ መንፈስና ሐሰተኛ መንፈስ
1ወዳጆች ሆይ! በዓለም ላይ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ስለ ተነሡ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ይልቅስ መንፈሶች የእግዚአብሔር መሆናቸውንና አለመሆናቸውን መርምሩ። 2የእግዚአብሔርን መንፈስ ለይታችሁ የምታውቁት በዚህ ነው፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡን የሚያምን መንፈስ ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ 3ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡን የማያምን መንፈስ ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ አይደለም፤ ይህም መንፈስ ይመጣል ሲባል የሰማችሁት የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው፤ እርሱ አሁን እንኳ በዓለም ላይ አለ።
4ልጆች ሆይ! እናንተ የእግዚአብሔር ናችሁ፤ በእናንተ ያለው መንፈስ በዓለም ካለው መንፈስ ይበልጣል። ስለዚህ ሐሰተኞች ነቢያትን አሸንፋችኋል። 5ሐሰተኞች ነቢያት የዓለም ናቸው፤ የሚናገሩትም የዓለምን ነገር ነው። ዓለምም እነርሱን ይሰማቸዋል። 6እኛ የእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ሁሉ ይሰማናል፤ የእግዚአብሔር ያልሆነ ግን አይሰማንም። እውነተኛን መንፈስና ሐሰተኛን መንፈስ ለይተን የምናውቀው በዚህ ነው።
እግዚአብሔር ፍቅር ነው
7ወዳጆች ሆይ! ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ እርስ በርሳችን እንፋቀር፤ የሚያፈቅር ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል። 8እግዚአብሔር ፍቅር ስለ ሆነ ሰውን የማያፈቅር ሁሉ እግዚአብሔርን አያውቅም። 9በልጁ አማካይነት ሕይወት እንድናገኝ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል፤ በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ መካከል ተገልጦአል። 10ፍቅር ማለት እንዲህ ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን ስለ ወደድነው ሳይሆን እርሱ ስለ ወደደንና ኃጢአታችንን እንዲደመስስ ልጁን ስለ ላከልን ነው።
11ወዳጆች ሆይ! እግዚአብሔር ይህን ያኽል ካፈቀረን እኛም እርስ በርሳችን መፋቀር ይገባናል። 12እግዚአብሔርን ያየው ማንም ሰው የለም። እኛ እርስ በርሳችን ብንፋቀር እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል፤ ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል። #ዮሐ. 1፥18።
13እግዚአብሔር መንፈሱን ስለ ሰጠን በእርሱ እንደምንኖርና እርሱም በእኛ እንደሚኖር እናውቃለን። 14አብ የዓለም አዳኝ አድርጎ ወልድን እንደ ላከው አይተናል፤ እንመሰክራለንም። 15ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚያምን ሰው ውስጥ እግዚአብሔር ይኖራል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። 16ስለዚህ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፤ እናምናለንም። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። 17በዚህ ዓለም እኛ የምንኖረው ልክ ክርስቶስ እንደሚኖረው እንደ መሆኑ ፍቅራችን ፍጹም ቢሆን በፍርድ ቀን ያለ ፍርሀት በፊቱ ለመቅረብ ሙሉ መተማመን ይኖረናል። 18ፍጹም ፍቅር ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ስለ ሆነ የሚፈራ ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።
19እግዚአብሔር አስቀድሞ ስላፈቀረን እኛም እናፈቅራለን። 20እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን የሚጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ከሆነ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወድ አይችልም። 21ስለዚህ ክርስቶስ የሰጠን ትእዛዝ እግዚአብሔርን የሚወድ ወንድሙንም ይውደድ የሚል ነው።
Currently Selected:
1 የዮሐንስ መልእክት 4: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997