አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 21
21
ዳዊት የሕዝብ ቈጠራ ማድረጉ
(2ሳሙ. 24፥1-25)
1ሰይጣን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ተነሥቶ ዳዊትን የሕዝብ ቈጠራ እንዲያደርግ አነሣሣው። 2ዳዊት ለኢዮአብና ለሌሎቹ የጦር መኰንኖች “በመላው እስራኤል ከአገሪቱ ዳር እስከ ዳር፥ ማለትም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ሄዳችሁ ሕዝቡን ቊጠሩ፤ እኔ በእስራኤል ምን ያኽል ሕዝብ እንዳለ ማወቅ እፈልጋለሁ” የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው።
3ኢዮአብም “ንጉሥ ሆይ፥ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ አሁን ካሉት ይልቅ በመቶ እጅ ያብዛልህ! እነርሱ በሙሉ የአንተ አገልጋዮች ናቸው፤ ታዲያ አንተ የሕዝብ ቈጠራ በማድረግ ሕዝቡን በሙሉ በደለኛ ለምን ታደርጋለህ?” አለ። 4ንጉሡ ግን ትእዛዙን እንዲፈጽም ኢዮአብን አስገደደው፤ ከዚህ በኋላ ኢዮአብ ከንጉሡ ፊት ወጣ፤ ሕዝቡንም ለመቊጠር በአገሪቱ በሙሉ ተዘዋውሮ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። 5ለውትድርና አገልግሎት ብቁ የሆኑትን ሰዎች ጠቅላላ ድምር ለዳዊት አስታወቀ፤ እነርሱም ከእስራኤል አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ሲሆኑ፥ ከይሁዳ ደግሞ አራት መቶ ሰባ ሺህ ነበሩ፤ 6ኢዮአብ በዚህ በንጉሡ ትእዛዝ ያልተስማማ በመሆኑ፥ የሌዊንና የብንያምን ነገዶች አልቈጠረም።
7እግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ እጅግ ስለ ተቈጣ እስራኤልን ቀጣ። 8ዳዊትም እግዚአብሔርን “እኔ ይህን በማድረጌ እጅግ ከባድ የሆነ ኃጢአት ሠርቼአለሁ! እባክህ ምሕረት አድርግልኝ፤ የስንፍና ሥራ ፈጽሜአለሁ!” አለው።
9በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የዳዊት ነቢይ የሆነውን ጋድን እንዲህ አለው፤ 10“ሄደህ ዳዊትን ‘እነሆ ሦስት ምርጫ ሰጥቼሃለሁ፤ እኔም አንተ የምትመርጠውን አደርጋለሁ’ ይላል” ብለህ ንገረው።
11ጋድም ወደ ዳዊት ሄዶ እግዚአብሔር ስለ እርሱ የተናገረውን ሁሉ ገለጠለት፤ እንዲህም ሲል ጠየቀው፤ 12“በምድርህ ላይ ሦስት ዓመት ራብ ከሚሆን ወይም ሦስት ወር ጠላቶችህ ከሚያሳድዱህ ወይም እግዚአብሔር በምድርህ ላይ ለሦስት ቀን በሰይፍ ከሚመታህና ቸነፈር በምድሪቱ ላይ አምጥቶ በእስራኤል ምድር ሁሉ በሞት የሚቀሥፍ መልአክ ከሚልክብህ የትኛውን ትመርጣለህ? እንግዲህ ወደ እግዚአብሔር የማቀርበውን መልስ ስጠኝ።”
13ዳዊትም “እነሆ እኔ ለምርጫ በሚያስቸግር ሁኔታ ላይ ነኝ! ይሁን እንጂ በሰው እጅ መውደቅ አልፈልግም፤ እግዚአብሔር መሐሪ ስለ ሆነ እርሱ ራሱ ይቅጣኝ” ሲል መለሰ።
14ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ቸነፈር አመጣ፤ ከሕዝቡም ሰባ ሺህ የሚሆኑት አለቁ፤ 15ቀጥሎም እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ መልአክ ልኮ ነበር፤ ነገር ግን ኢየሩሳሌምን ማጥፋት እንደ ጀመረ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ያደረሰው ችግር አሳዝኖት መልአኩን “እስከ አሁን የደረሰባቸው ችግር ይበቃልና አቁም!” አለው። በዚያን ጊዜ መልአኩ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።
16ዳዊትም መልአኩ ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ ሰይፉን በእጁ እንደ ያዘ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ አየው፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ማቅ ለብሰው የነበሩት የሕዝቡ አለቆች በሙሉ በግንባራቸው በመሬት ላይ ተደፉ። 17ዳዊትም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ በደል የፈጸምኩት እኔ ነኝ፤ ሕዝቡ እንዲቈጠር ትእዛዝ ያስተላለፍኩትም እኔ ነኝ፤ ታዲያ እነዚህ አሳዛኝ ሕዝብህ ምን አደረጉ? እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እኔንና ቤተሰቤን ቅጣ እንጂ በሕዝብህ ላይ ይህንን መቅሠፍት አታውርድ።”
18የእግዚአብሔር መልአክ ጋድን “ዳዊት ወደ ኢያቡሳዊው ወደ ኦርና አውድማ ሄዶ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንዲሠራ ንገረው” አለው፤ 19ዳዊትም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመፈጸም ጋድ እንደ ነገረው ለማድረግ ሄደ፤ 20በዚያም አውድማ ላይ ራሱ ኦርናና አራት ወንዶች ልጆቹ ስንዴ ይወቁ ነበር፤ መልአኩንም ባዩ ጊዜ ልጆቹ ሮጠው ተደበቁ። 21ኦርናም ዳዊት ወደ እነርሱ እየቀረበ መምጣቱን ባየ ጊዜ ከአውድማው ወጥቶ ወደ መሬት ለጥ በማለት እጅ ነሣ፤ 22ዳዊትም “ቸነፈሩ ይወገድ ዘንድ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንድሠራበት አውድማህን ሽጥልኝ፤ እኔም ሙሉ ዋጋ እሰጥሃለሁ” አለው።
23ኦርናም “ንጉሥ ሆይ፥ ውሰደው፤ የፈለግኸውንም አድርግበት፤ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት ሆነው እንዲቃጠሉ እነዚህን በሬዎች ጨምረህ ውሰድ፤ እነዚህም የእህል መውቂያ እንጨቶች ለማገዶ ይሁኑልህ፤ ስንዴውንም መባ አድርገህ አቅርበው፤ እነሆ ሁሉንም ለአንተ ሰጥቼሃለሁ” አለው።
24ንጉሥ ዳዊት ግን “ይህስ አይሆንም፤ ሙሉውን ዋጋ እከፍልሃለሁ፤ የአንተ ንብረት የሆነውን፥ እኔ ምንም ዋጋ ያልከፈልኩበትን ነገር ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጌ ማቅረብ አልፈልግም” ሲል መለሰለት። 25ለኦርናም የአውድማውን ሒሳብ ስድስት መቶ ከወርቅ የተሠራ ገንዘብ ሰጠው፤ 26ዳዊት በዚያ ስፍራ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠርቶ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ፤ በጸለየም ጊዜ እግዚአብሔር በመሠዊያው ላይ የነበረውን መሥዋዕት የሚበላ እሳት ከሰማይ በመላክ ለጸሎቱ መልስ ሰጠው።
27እግዚአብሔርም መልአኩን “ሰይፍህን ወደ አፎቱ መልስ” አለው፤ መልአኩም እንደታዘዘው አደረገ፤ 28በዚህም ሁኔታ እግዚአብሔር ጸሎቱን የሰማለት መሆኑን ዳዊት ተገነዘበ፤ ስለዚህም በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በሚገኘው መሠዊያ ላይ እንደገና መሥዋዕት አቀረበ፤ 29ሙሴ በበረሓ የሠራው እግዚአብሔር የሚመለክበት ድንኳንና መሥዋዕት ይቀርብበት የነበረው መሠዊያ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በገባዖን በሚገኘው የማምለኪያ ስፍራ ይገኛሉ፤ 30ነገር ግን ዳዊት የእግዚአብሔርን መልአክ ሰይፍ ስለ ፈራ ወደዚያ ሄዶ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ አልቻለም።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 21: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997