አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 20
20
ዳዊት ራባ ተብላ የምትጠራውን ከተማ በድል አድራጊነት መያዙ
(2ሳሙ. 12፥26-31)
1በተከታዩ የዓመት መባቻ ማለትም ነገሥታት አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጦርነት በሚሄዱበት ወራት፥ ኢዮአብ ሠራዊቱን እየመራ ሄዶ የዐሞንን አገር ወረረ፤ ንጉሥ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፤ የኢዮአብ ሠራዊትም የራባን ከተማ ከበው አደጋ በመጣል ደመሰሱአት፤ #2ሳሙ. 11፥1። 2ሚልኮም ተብሎ የሚጠራው የዐሞናውያን ጣዖት ሠላሳ አራት ኪሎ ያኽል የሚመዝን ዘውድ ነበረው፤ በውስጡም የከበረ ዕንቊ ነበር፤ ዳዊት ያንን ዘውድ ወስዶ በራሱ ላይ ደፋ፤ እንዲሁም ከከተማይቱ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤ #20፥2 ሚልኮም ተብሎ የሚጠራው የዐሞናውያን ጣዖት፦ ወይም የዐሞናውያን ንጉሥ። 3የከተማይቱንም ሕዝብ ማርኮ በመጋዝ፥ በዶማና በመጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ በዐሞን በሚገኙ በሌሎች ታናናሽ ከተማዎች የሚኖሩትንም ሰዎች በዚሁ ዐይነት እንዲሠሩ አደረገ፤ ከዚያም በኋላ እርሱና ሠራዊቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
በፍልስጥኤማውያን ኀያላን ሰዎች ላይ የተደረገ ጦርነት
(2ሳሙ. 21፥15-22)
4ዘግየት ብሎም በጌዜር የሚኖሩ ፍልስጥኤማውያን ላይ ጦርነት ተደረገ፤ በዚያን ጊዜ የሑሻ ተወላጅ የሆነው ሲበካይ፥ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሲፓይ ተብሎ የሚጠራውን ኀያል ሰው ገደለ፤ ፍልስጥኤማውያንም ተሸነፉ።
5በፍልስጥኤማውያን ላይ የተደረገ ሌላም ጦርነት ነበረ፤ በዚያን ጊዜ የያዒር ልጅ ኤልሐናን የጋት ተወላጅ የሆነውን የጦሩ እጀታ ውፍረቱ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጎልያድን ወንድም ላሕሚን ገደለ። #1ሳሙ. 17፥4-7።
6ሌላም ጦርነት በጋት ተደረገ፤ በዚያም ጦርነት በእያንዳንዱ እጅና በእያንዳንዱ እግር ላይ ስድስት ስድስት በጠቅላላ ኻያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ረጅም ሰው ነበር፤ እርሱም ኀያላን ከሆኑት ከራፋይም ዘር ነበር፤ 7ይህም ሰው እስራኤላውያንን ተገዳደረ፤ እርሱንም የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ዮናታን ገደለው።
8በዳዊትና በሠራዊቱ የተገደሉት እነዚህ ሦስቱ ሰዎች ኀያላን ከሆኑት የራፋይም ዘር ነበሩ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 20: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997