YouVersion Logo
Search Icon

ራእይ 5

5
ጥቅልል መጽሐፉና በጉ
1በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው በውስጥና በውጭ በኩል የተጻፈበት፣ በሰባት ማኅተም የታሸገ ጥቅልል መጽሐፍ በቀኝ እጁ ይዞ አየሁ። 2አንድ ብርቱ መልአክ በታላቅ ድምፅ፣ “ማኅተሞቹን ለመፍታትና መጽሐፉን ለመክፈት የተገባው ማን ነው?” ብሎ ሲያውጅ አየሁ። 3ነገር ግን በሰማይም ሆነ በምድር፣ ከምድርም በታች መጽሐፉን ለመክፈት ወይም ገልጦ ለመመልከት የሚችል ማንም አልነበረም። 4እኔም መጽሐፉን ለመክፈት ወይም ገልጦ ለመመልከት የተገባው ማንም ባለመኖሩ እጅግ አለቀስሁ። 5ከዚያም ከሽማግሌዎቹ አንዱ፣ “አታልቅስ፤ እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር ድል ነሥቷል፤ እርሱ መጽሐፉን ሊከፍትና ሰባቱንም ማኅተሞች ሊፈታ ይችላል” አለኝ።
6ከዚያም በዙፋኑና በአራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ በሽማግሌዎቹም መካከል የታረደ የሚመስል በግ ቆሞ አየሁ፤ በጉም ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩት ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት#5፥6 ወይም ሰባት ዕጥፍ መንፈስ ናቸው። 7እርሱም መጥቶ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ቀኝ እጅ መጽሐፉን ወሰደ። 8መጽሐፉን በወሰደ ጊዜ አራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም በበጉ ፊት በግንባራቸው ተደፉ፤ እያንዳንዳቸውም የቅዱሳን ጸሎት የሆኑትን በገናና ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ሙዳይ ይዘው ነበር። 9እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤
“መጽሐፉን ልትወስድ፣
ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤
ምክንያቱም ታርደሃል፤
በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣
ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።
10ለአምላካችንም መንግሥትና ካህናት አድርገሃቸዋል፤
እነርሱም በምድር ላይ ይነግሣሉ።”
11ከዚያም ተመለከትሁ፤ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም ሺሕ ጊዜ ሺሕና እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ። እነርሱም በዙፋኑና በሕያዋን ፍጡራኑ፣ በሽማግሌዎቹም ዙሪያ ከብበው ነበር፤ 12በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ዘመሩ፤
“የታረደው በግ ኀይልና ባለጠግነት፣
ጥበብና ብርታት፣
ክብርና ሞገስ፣ ምስጋናም፣
ሊቀበል ይገባዋል።”
13ከዚያም በሰማይና በምድር፣ ከምድር በታችና በባሕር፣ በእነርሱ ውስጥ ያሉ ፍጡራንም ሁሉ እንዲህ ብለው ሲዘምሩ ሰማሁ፤
“በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ፣
ምስጋናና ሞገስ፣ ክብርና ኀይል፣
ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን!”
14አራቱ ሕያዋን ፍጡራንም፣ “አሜን!” አሉ፤ ሽማግሌዎቹም በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ።

Currently Selected:

ራእይ 5: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in