ራእይ 11
11
ሁለቱ ምስክሮች
1ከዚያም ሸንበቆ የመሰለ መለኪያ በትር ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልሁ፤ “ሄደህ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና መሠዊያውን ለካ፤ በዚያም የሚያመልኩትን ቍጠር። 2የውጭውን አደባባይ ግን ተወው አትለካው፣ ለአሕዛብ የተሰጠ ነውና። እነርሱ የተቀደሰችውን ከተማ አርባ ሁለት ወር ይረግጧታል። 3ለሁለቱ ምስክሮቼ ኀይል እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ማቅ ለብሰው አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ይናገራሉ።” 4እነዚህም በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙት ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። 5ማንም እነርሱን ሊጐዳ ቢፈልግ፣ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ያጠፋል፤ ሊጐዳቸው የሚፈልግ ሁሉ መሞት ያለበት በዚህ ዐይነት ነው። 6እነዚህ ሰዎች ትንቢት በሚናገሩባቸው ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ለመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ ደግሞም ውሆችን ወደ ደም ለመለወጥ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ ምድርን በማንኛውም መቅሠፍት ለመምታት ሥልጣን አላቸው።
7ምስክርነታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ድል ይነሣቸዋል፤ ይገድላቸዋልም። 8ሬሳቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይጣላል፤ ይህች ከተማ ሰዶምና ግብፅ እየተባለች በምሳሌ የምትጠራውና የእነርሱም ጌታ የተሰቀለባት ናት። 9ከወገን፣ ከነገድ፣ ከቋንቋና ከሕዝብ የመጡ ሰዎች ሬሳቸውን ሦስት ቀን ተኩል ይመለከታሉ፤ ሬሳቸውም እንዳይቀበር ይከለክላሉ። 10እነዚህ ሁለት ነቢያት የምድር ነዋሪዎችን ያሠቃዩ ስለ ነበር፣ በምድር የሚኖሩ ሰዎች በእነርሱ ላይ በደረሰው ደስ ይላቸዋል፤ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይለዋወጣሉ።
11ከሦስቱ ቀን ተኩል በኋላ ግን፣ የሕይወት እስትንፋስ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶ ገባባቸው፤ እነርሱም ተነሥተው በእግሮቻቸው ቆሙ፤ ይመለከቷቸውም በነበሩት ላይ ታላቅ ድንጋጤ ወረደባቸው። 12ከዚያም፣ “ወደዚህ ውጡ” የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸው እየተመለከቷቸው በደመና ወደ ሰማይ ወጡ።
13በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የከተማዪቱም አንድ ዐሥረኛ ወደመ፤ በነውጡም ሰባት ሺሕ ሰዎች ሞቱ፤ የተረፉትንም ፍርሀት ያዛቸው፤ ለሰማይም አምላክ ክብር ሰጡ።
14ሁለተኛው ወዮ ዐልፏል፤ እነሆ፤ ሦስተኛው ወዮ ቶሎ ይመጣል።
ሰባተኛው መለከት
15ሰባተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በሰማይም እንዲህ የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ፤
“የዓለም መንግሥት፣
የጌታችንና የእርሱ ክርስቶስ መንግሥት ሆነች፤
እርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”
16በእግዚአብሔር ፊት በዙፋኖቻቸው ላይ የተቀመጡት ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ 17እንዲህም አሉ፤
“ያለህና የነበርህ፣
ሁሉን ቻይ፣
ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እናመሰግንሃለን፤
ምክንያቱም አንተ ታላቁን ኀይልህን ይዘህ ነግሠሃል።
18አሕዛብ ተቈጥተው ነበር፤
የአንተም ቍጣ መጣች፤
በሙታን ላይ የምትፈርድበት፣
ለአገልጋዮችህ ለነቢያት፣
ለቅዱሳንና ስምህን ለሚፈሩት፣
ለታናናሾችና ለታላላቆች ዋጋቸውን የምትሰጥበት፣
ምድርንም ያጠፏትን የምታጠፋበት ዘመን መጣ።”
19ከዚያም በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተከፈተ፤ በመቅደሱም ውስጥ የኪዳኑ ታቦት ታየ፤ መብረቅ፣ ድምፅ፣ ነጐድጓድ፣ የምድር መናወጥና ታላቅም በረዶ ሆነ።
Currently Selected:
ራእይ 11: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.