መዝሙር 72
72
መዝሙር 72
በተስፋ የሚጠባበቀው ንጉሥ
ስለ ሰሎሞን።
1እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍትሕን ለንጉሥ፣
ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ ዐድል፤
2እርሱም ሕዝብህን በጽድቅ ይዳኛል፤#72፥2 ወይም እርሱ ሕዝቡን በጽድቅ ይዳኝ
ለተቸገሩትም በትክክል ይፈርዳል።
3ተራሮች ብልጽግናን፣
ኰረብቶችም የጽድቅን ፍሬ ለሕዝቡ ያመጣሉ።
4ለተቸገረው ሕዝብ ይሟገታል፤
የድኾችን ልጆች ያድናል፤
ጨቋኙንም ያደቅቀዋል።
5ፀሓይ እስካለች ድረስ፣
ጨረቃም በምትኖርበት ዘመን ሁሉ፣ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።#72፥5 ወይም የተፈራ ይሆናል
6እንደ ዝናብ በታጨደ መስክ ላይ ይወርዳል፤
እንደ ካፊያም ምድርን ያረሰርሳል።
7በዘመኑ ጽድቅ ይሰፍናል፤
ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም ሰላም ይበዛል።
8ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣
ከታላቁም ወንዝ#72፥8 የኤፍራጥስ ወንዝ ነው። እስከ ምድር ዳርቻ ይገዛል።
9የበረሓ ዘላኖች በፊቱ ይሰግዳሉ፤
ጠላቶቹም ዐፈር ይልሳሉ።
10የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት፣
ግብር ያመጡለታል፤
የዐረብና የሳባ ነገሥታት፣
እጅ መንሻ ያቀርባሉ።
11ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል፤
ሕዝቦችም ሁሉ ይገዙለታል።
12ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣
ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል።
13ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤
ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል።
14ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል፤
ደማቸውም በእርሱ ፊት ክቡር ነው።
15ዕድሜው ይርዘም!
ከዐረብ ወርቅ ይምጣለት፤
ዘወትር ይጸልዩለት፤
ቀኑንም ሙሉ ይባርኩት።
16በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤
በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ።
ፍሬው እንደ ሊባኖስ ይንዠርገግ፤
በከተማ ያለውም እንደ ሜዳ ሣር እጅብ ብሎ ይውጣ።
17ስሙ ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤
ዝናው ፀሓይ የምትኖረውን ዘመን ያህል ይዝለቅ።
ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ ይባረኩ፤
ሕዝቡ ሁሉ ቡሩክ ነህ ይበለው።
18ብቻውን ድንቅ ነገር የሚያደርግ፣
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ።
19ክቡር ስሙ ለዘላለም ይባረክ፤
ምድርም ሁሉ በክብሩ ይሞላ።
አሜን፤ አሜን።
20የእሴይ ልጅ የዳዊት ጸሎት እዚህ ላይ ተፈጸመ።
Currently Selected:
መዝሙር 72: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.