YouVersion Logo
Search Icon

መዝሙር 65

65
መዝሙር 65
የምስጋና መዝሙር
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት የምስጋና መዝሙር።
1እግዚአብሔር ሆይ፤ በጽዮን ለአንተ ውዳሴ ይገባል፤#65፥1 በዕብራይስጡ የዚህ ቃል ትርጉም በትክክል አይታወቅም።
ለአንተ የተሳልነውን እንፈጽማለን።
2ጸሎትን የምትሰማ ሆይ፤
የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ።
3ኀጢአት ባጥለቀለቀን ጊዜ፣
አንተ መተላለፋችንን ይቅር አልህ።#65፥3 ወይም አንተ ተቤዠኸን
4አንተ የመረጥኸው፣ ወደ ራስህ ያቀረብኸው፣
በአደባባይህም ያኖርኸው ምስጉን ነው!
ከተቀደሰው መቅደስህ፣
ከቤትህም በረከት እንረካለን።
5እግዚአብሔር አዳኛችን ሆይ፤
በጽድቅ ድንቅ አሠራር መልስልን፤
አንተ ለምድር ዳርቻ ሁሉ፣
በርቀት ላለውም ባሕር ተስፋ ነህ።
6ተራሮችን በብርታትህ መሠረትህ፤
ኀይልንም ታጥቀሃል።
7አንተ የባሕሮችን ማስገምገም፣
የማዕበላቸውን ፉጨት፣
የሕዝቦችንም ሁከት ጸጥ ታደርጋለህ።
8ርቀው በምድር ዳርቻ ያሉት ከድንቅ ሥራህ የተነሣ ይደነግጣሉ፤
የንጋትንና የምሽትን መምጫዎች፣
በደስታ እልል እንዲሉ ታደርጋቸዋለህ።
9ምድርን ትጐበኛለህ፤ ታጠጣለህም፤
እጅግ ታበለጥጋታለህም።
ለሰዎች እህልን ይለግሱ ዘንድ፣
የእግዚአብሔር ወንዞች ውሃን የተሞሉ ናቸው፤
አንተ እንዲህ እንዲሆን ወስነሃልና።#65፥9 ወይም “አንተም ለዚህ ነው ምድርን ያዘጋጀሃት”
10ትልሟን በውሃ ታረሰርሳለህ፤
ቦይዋን ታስተካክላለህ፤
በካፊያ ታለሰልሳለህ፤
ቡቃያዋንም ትባርካለህ።
11ለዘመኑ በጎነትህን ታጐናጽፈዋለህ፤
ሠረገላህም በረከትን ተሞልቶ ይፈስሳል።
12የምድረ በዳው ሣር እጅግ ለመለመ፤
ኰረብቶችም ደስታን ተጐናጸፉ።
13ሜዳዎች መንጋ በመንጋ ሆኑ፤
ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤
እልል ይላሉ፤ ይዘምራሉም።

Currently Selected:

መዝሙር 65: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in