YouVersion Logo
Search Icon

መዝሙር 39

39
መዝሙር 39
ታላቅ እግዚአብሔር-ታናሽ ሰው
ለመዘምራን አለቃ፣ ለኤዶታም፤ የዳዊት መዝሙር።
1እኔ፣ “በአንደበቴ እንዳልበድል፣
መንገዴን እጠብቃለሁ፤
ክፉዎችም በእኔ ዘንድ እስካሉ ድረስ፣
ልጓም በአፌ አስገባለሁ” አልሁ።
2እንደ ዲዳ ዝም አልሁ፤
ለበጎ ነገር እንኳ አፌን ዘጋሁ፤
ሆኖም ጭንቀቴ ባሰ።
3ልቤ በውስጤ ጋለ፤
በማሰላስልበትም ጊዜ እሳቱ ነደደ፤
ከዚያም በአንደበቴ እንዲህ ተናገርሁ፤
4እግዚአብሔር ሆይ፤ የሕይወቴን ፍጻሜ፣
የዘመኔንም ቍጥር አስታውቀኝ፤
ዐላፊ ጠፊ መሆኑንም ልረዳ።
5እነሆ፤ ዘመኔን በስንዝር ለክተህ አስቀመጥህ፤
ዕድሜዬም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው፤
በርግጥ የሰው ሁሉ ሕይወት ተን ነው። ሴላ
6“ሰው የጥላ ውልብታ ነው፤
በከንቱም ይታወካል፤
ለማን እንደሚሆን ሳያውቅ ሀብት ንብረት ያከማቻል።
7“ጌታ ሆይ፤ አሁንስ ወደ ማን ልመልከት?
ተስፋዬ በአንተ ላይ ነው።
8ከኀጢአቴ ሁሉ አድነኝ፤
የሰነፎች መሣለቂያ አታድርገኝ።
9ይህን ያደረግህ አንተ ነህና፣
ዝም እላለሁ፤ አፌንም አልከፍትም።
10ክንድህን አንሣልኝ፤
ከእጅህ ምት የተነሣ ደክሜአለሁ።
11ሰዎችን ስለ ኀጢአታቸው ለመቅጣት ትገሥጻቸዋለህ፤
ሀብታቸውንም ብል እንደ በላው ታደርጋለህ፤
በርግጥ ሰው ሁሉ ተን ብቻ ነው። ሴላ
12እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማ፤
ጩኸቴን አድምጥ፤
ልቅሶዬንም ቸል አትበል፤
በአንተ ፊት እኔ መጻተኛ ነኝና፤
እንደ አባቶቼም እንግዳ ነኝ።
13ላለመመለስ ከመሰናበቴ በፊት፣
ዳግመኛ ደስ ይለኝ ዘንድ ዐይንህን ከላዬ አንሣ።”

Currently Selected:

መዝሙር 39: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in