መዝሙር 34
34
መዝሙር 34#34 34 የዚህ መዝሙር እያንዳንዱ ጥቅስ ተከታታይ ፊደላት ባሉት የዕብራይስጥ ሆህያት የሚጀመር ሲሆን፣ ጅማሬው ወይም ጅማሬውና መጨረሻው ትርጕም የሚሰጥ ግጥም ነው።
የእግዚአብሔር ፍትሕ ውዳሴ
እንደ እብድ ሆኖ አቤሜሌክ ፊት በመቅረቡ ተባርሮ በወጣ ጊዜ የዘመረው፤ የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፤
ምስጋናውም ዘወትር ከአፌ አይለይም።
2ነፍሴ በእግዚአብሔር ተመካች፤
ትሑታንም ይህን ሰምተው ሐሤት ያደርጋሉ።
3ኑና ከእኔ ጋር እግዚአብሔርን አክብሩት፤
ስሙንም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ።
4 እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እርሱም መለሰልኝ፤
ከፍርሀቴም ሁሉ አዳነኝ።
5ወደ እርሱ የሚመለከቱ ያበራሉ፤
ፊታቸውም ከቶ አያፍርም።
6ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤
ከመከራውም ሁሉ አዳነው።
7 እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤
ያድናቸዋልም።
8 እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ፤
እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ቡሩክ ነው!
9እናንተ ቅዱሳኑ፤ እግዚአብሔርን ፍሩት፤
እርሱን የሚፈሩት አንዳች አያጡምና።
10አንበሶች ሊያጡ፣ ሊራቡም ይችላሉ፤
እግዚአብሔርን የሚሹ ግን መልካም ነገር አይጐድልባቸውም።
11ልጆቼ ሆይ፣ ኑ፤ ስሙኝ፤
እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ።
12ሕይወትን የሚወድድ፣
በጎውንም ያይ ዘንድ ዕድሜን የሚመኝ ማን ነው?
13አንደበትህን ከክፉ ነገር ከልክል፤
ከንፈርህንም ከሽንገላ ጠብቅ።
14ከክፉ ሽሽ፤ መልካሙንም አድርግ፤
ሰላምን ፈልጋት፤ ተከተላትም።
15 የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤
ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው።
16መታሰቢያቸውን ከምድር ለማጥፋት፣
የእግዚአብሔር ፊት በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።
17ጻድቃን ሲጮኹ፣ እግዚአብሔር ይሰማቸዋል፤
ከመከራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል።
18 እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤
መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።
19የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤
እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል።
20ዐጥንቶቹን ሁሉ ይጠብቃል፤
ከእነርሱም አንድ አይሰበርም።
21ኀጢአተኞችን ክፋት ይገድላቸዋል፤
ጻድቃንን የሚጠሉ ይፈረድባቸዋል።
22 እግዚአብሔር የባሪያዎቹን ነፍስ ይቤዣል፤
እርሱንም መጠጊያ ያደረገ አይፈረድበትም።
Currently Selected:
መዝሙር 34: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.