ምሳሌ 17
17
1ጠብ እያለ ግብዣ#17፥1 ዕብራይስጡ መሥዋዕት ይላል። ከሞላበት ቤት ይልቅ፣
በሰላምና በጸጥታ ድርቆሽ ይሻላል።
2ጠቢብ አገልጋይ በወራዳ ልጅ ላይ ሥልጣን ይኖረዋል፤
ከወንድማማቾቹም እንደ አንዱ ውርስ ይካፈላል።
3ብር በማቅለጫ፣ ወርቅም በከውር፤
እግዚአብሔርም ልብን ይፈትናል።
4እኩይ ሰው ክፉ ንግግር ያዳምጣል፤
ሐሰተኛም የተንኰለኛን አንደበት በጥንቃቄ ይሰማል።
5በድኾች የሚያፌዝ ፈጣሪያቸውን ይንቃል፤
በሌላው ሰው መከራ ደስ የሚለው ከቅጣት አያመልጥም።
6የልጅ ልጆች ለአረጋውያን ዘውድ ናቸው፤
ወላጆችም ለልጆቻቸው አለኝታ ናቸው።
7መልካም አነጋገር#17፥7 ወይም የኵራት አነጋገር ለሞኝ አይሰምርለትም፤
ለገዥ ሐሰተኛ አንደበት የቱን ያህል የከፋ ይሆን!
8እጅ መንሻ ለሰጪው እንደ ድግምት ዕቃ ነው፤
በሄደበትም ቦታ ሁሉ ይሳካለታል።
9በደልን የሚሸፍን ፍቅርን ያዳብራል፤
ነገርን የሚደጋግም ግን የልብ ወዳጆችን ይለያያል።
10መቶ ግርፋት ሞኝን ከሚሰማው ይልቅ፣
ተግሣጽ ለአስተዋይ ጠልቆ ይሰማል።
11ክፉ ሰው ዐመፅን ብቻ ይፈልጋል፤
በርሱም ላይ ጨካኝ መልእክተኛ ይላክበታል።
12ሞኝን በቂልነቱ ከመገናኘት፣
ግልገሎቿን የተነጠቀችን ድብ መጋፈጥ ይሻላል።
13በበጎ ፈንታ ክፉ የሚመልስ ሰው፣
ክፉ ነገር ከቤቱ አይርቅም።
14ጠብ መጫር ግድብን እንደ መሸንቈር ነው፤
ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ።
15በደለኛውን ማጽደቅ ሆነ፣ ጻድቁን በደለኛ ማድረግ፣
ሁለቱም በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናቸው።
16ጥበብን ለማግኘት ፍላጎት ስለሌለው፣
ሞኝ እጅ የገባ ገንዘብ ጥቅሙ ምንድን ነው?
17ወዳጅ ምን ጊዜም ወዳጅ ነው፤
ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል።
18ልበ ቢስ ሰው ሰው ቃል በመግባት እጅ ይመታል፤
ለወዳጁም ዋስ ይሆናል።
19ጠብ የሚወድድ ኀጢአትን ይወድዳል፤
በሩን ከፍ አድርጎ የሚሠራም ጥፋትን ይጋብዛል።
20ጠማማ ልብ ያለው ሰው አይሳካለትም፤
በአንደበቱ የሚቀላምድም መከራ ላይ ይወድቃል።
21ሞኝ ልጅ መውለድ ሐዘን ያስከትላል፤
የተላላም አባት ደስታ የለውም።
22ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው፤
የተሰበረ መንፈስ ግን ዐጥንትን ያደርቃል።
23ክፉ ሰው ፍትሕ ለማዛባት፣
በስውር ጕቦ ይቀበላል።
24አስተዋይ ሰው ጥበብን ከፊቱ አይለያትም፤
የሞኝ ዐይኖች ግን እስከ ምድር ዳርቻ ይንከራተታሉ።
25ሞኝ ልጅ በአባቱ ላይ ሐዘን ያስከትላል፤
ለወለደችውም ምሬት ይሆንባታል።
26ንጹሑን ሰው መቅጣት ተገቢ አይደለም፤
ሹሞችን ስለ ቅንነታቸው መግረፍ መልካም አይደለም።
27ዐዋቂ ሰው ንግግሩ ቍጥብ ነው፤
አስተዋይም መንፈሱ የረጋ ነው።
28ቂል እንኳ ዝም ቢል ጠቢብ፣
አንደበቱንም ቢገዛ አስተዋይ ይመስላል።
Currently Selected:
ምሳሌ 17: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.