ዘኍል 27
27
የሰለጰዓድ ሴት ልጆች
1የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የገለዓድ ልጅ፣ የአፌር ልጅ፣ የሰለጰዓድ ሴት ልጆች ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ጐሣዎች ነበሩ፤ ስማቸውም ማህለህ፣ ኑዓ፣ ዔግላ፣ ሚልካና ቲርጻ ይባላል። እነርሱም፣ 2ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ ቀረቡ፤ በሙሴ፣ በካህኑ በአልዓዛር፣ በመሪዎችና በመላው ማኅበርም ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፤ 3“አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ ተባብረው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ ካመፁት ከቆሬ ተከታዮች ጋር አልነበረም፤ የሞተው ግን በራሱ ኀጢአት ሲሆን፣ ወንዶች ልጆችም አልነበሩትም። 4ታዲያ አባታችን ወንድ ልጅ ባለመውለዱ ስሙ ከጐሣዎቹ ተለይቶ እንዴት ይጠፋል? ለእኛም በአባታችን ዘመዶች መካከል ርስት ስጡን።”
5ስለዚህ ሙሴ ጕዳያቸውን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) አቀረበ፤ 6እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ 7“የሰለጰዓድ ልጆች ጥያቄ ትክክል ነው፤ በርግጥ በአባታቸው ዘመዶች መካከል ድርሻቸውን ርስት አድርገህ ልትሰጣቸው ስለሚገባ የአባታቸውን ድርሻ ለእነርሱ አስተላልፍላቸው።
8“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘አንድ ሰው ወንድ ልጅ ሳይተካ ቢሞት ውርሱን ለሴት ልጁ አስተላልፉ። 9ሴት ልጅ ከሌለችው ደግሞ ውርሱን ለወንድሞቹ ስጡ። 10ወንድሞች ከሌሉትም ውርሱን ለአባቱ ወንድሞች ስጡ። 11አባቱ፣ ወንድሞች ከሌሉት ውርሱን ከጐሣው መካከል ቅርብ ለሆነ ዘመዱ ይስጥ፤ እርሱም ይውረሰው። ይህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤላውያን ሕጋዊ መመሪያ ይሆናቸዋል።’ ”
ኢያሱ በሙሴ እግር ተተካ
12ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በዓባሪም ሸንተረር ላይ ወዳለው ወደዚህ ተራራ ውጣና ለእስራኤላውያን የሰጠኋቸውን ምድር እይ። 13ካየኸውም በኋላ አንተም እንደ ወንድምህ እንደ አሮን ወደ ሕዝብህ ትሰበሰባለህ፤ 14ምክንያቱም ማኅብረ ሰቡ በጺን ምድረ በዳ ባለው ውሃ አጠገብ ባመፁ ጊዜ እኔን በሕዝቡ ፊት ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ሁለታችሁም ትእዛዜን ስላልጠበቃችሁ ነው።” ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ የሚገኝ የመሪባ ውሃ ነው።
15ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ 16“የሰብአዊ ፍጡር ሁሉ መንፈስ አምላክ (ኤሎሂም) የሆነ ጌታ እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህ ማኅበረ ሰብ ላይ ሰው ይሹም፤ 17እርሱም፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሕዝብ እረኛ እንደሌለው የበግ መንጋ እንዳይሆን በፊቱ የሚወጣና የሚገባ፣ መርቶ የሚያወጣውና የሚያገባው እንዲሆን ነው።”
18ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “መንፈስ ቅዱስ#27፥18 ወይም መንፈስ ያደረበትን የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን ጫንበት። 19በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበር ፊት እንዲቆም አድርገው፤ በፊታቸውም ሹመው፤ 20መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ እንዲታዘዝለትም ከሥልጣንህ ከፍለህ ስጠው። 21እርሱም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሆኖ በኡሪም በመጠየቅ ውሳኔ በሚያስገኝለት በካህኑ በአልዓዛር ፊት ይቆማል፤ እርሱም ሆነ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ በአልዓዛር ትእዛዝ ይወጣሉ፤ በእርሱም ቃል ይገባሉ።”
22ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በመላው የእስራኤል ማኅበር ፊት አቆመው፤ 23ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት ባዘዘው መሠረት እጁን በራሱ ላይ ጭኖ ሾመው።
Currently Selected:
ዘኍል 27: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.