YouVersion Logo
Search Icon

ማቴዎስ 6

6
ስለ ምጽዋት አሰጣጥ
1 “ሰዎች እንዲያዩላችሁ፣ መልካም ሥራችሁን በፊታቸው ከማድረግ ተጠንቀቁ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ከሰማዩ አባታችሁ ዋጋ አታገኙም።
2 “ግብዞች በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለው በየጐዳናውና በየምኵራቡ እንደሚያደርጉት፣ አንተም ለድኾች ምጽዋት በምትሰጥበት ጊዜ ይታይልኝ ብለህ ጥሩንባ አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። 3እናንተ ግን ለድኾች ስትሰጡ፣ ቀኝ እጃችሁ የሚያደርገውን ግራ እጃችሁ አይወቅ፤ 4ምጽዋታችሁ በስውር ይሁን፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባታችሁም ዋጋችሁን ይከፍላችኋል።
ስለ ጸሎት
6፥9-13 ተጓ ምብ – ሉቃ 11፥2-4
5 “ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ እነርሱ ለሰዎች ለመታየት ሲሉ በየምኵራቡና በየመንገዱ ማእዘን ላይ ቆመው መጸለይ ይወድዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ሙሉ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። 6አንተ ግን ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በሩንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል። 7ስትጸልዩ፣ ከንቱ ቃላት በመደጋገም ጸሎታቸው የሚሰማላቸው እንደሚመስላቸው አሕዛብ ነገራችሁን አታስረዝሙ። 8እነርሱን አትምሰሏቸው፤ አባታችሁ ከመለመናችሁ በፊት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃልና።
9 “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤
“ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤
ስምህ ይቀደስ፤
10 መንግሥትህ ትምጣ፤
ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣
እንዲሁ በምድር ትሁን።
11 የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን።
12 እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣
በደላችንን ይቅር በለን።
13 ወደ ፈተናም አታግባን
ከክፉው አድነን እንጂ፤
መንግሥት፣ ኃይል፣ ክብርም
ለዘለዓለሙ ያንተ ነውና፤ አሜን። # 6፥13 በግሪኩ ይህ የለም፤ ሆኖም በሌሎቹ የጥንት ትርጕሞች ይገኛል።
14 እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። 15ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም።
ስለ ጾም
16 “ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ መጾማቸው እንዲታወቅላቸው ሆን ብለው በፊታቸው ላይ የሐዘን ምልክት ያሳያሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። 17አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤ 18በዚህም መጾምህ በስውር ያለው አባትህ ብቻ የሚያውቀው፣ ከሰዎች ግን የተሰወረ ይሆናል፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል።
ሰማያዊ ሀብት
6፥2223 ተጓ ምብ – ሉቃ 11፥34-36
19 “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። 20ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤ 21ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና።
22 “ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። 23ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን?
24 “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።
አለመጨነቅ
6፥25-33 ተጓ ምብ – ሉቃ 12፥22-31
25 “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሯችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን? 26እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? 27ለመሆኑ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት#6፥27 ወይም በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል አለን?
28 “ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም። 29ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ያን ያህል ክብር የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዲቱ አልለበሰም። 30እናንተ እምነት የጐደላችሁ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ በነጋታው እሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር ይህን ያህል ካለበሰ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? 31ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ 32አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ይጨነቃሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። 33ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል። 34ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና።

Currently Selected:

ማቴዎስ 6: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy