ማቴዎስ 28
28
የኢየሱስ ከሙታን መነሣት
28፥1-8 ተጓ ምብ – ማር 16፥1-8፤ ሉቃ 24፥1-10
1ሰንበት ካለፈ በኋላ፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ጎሕ ሲቀድድ፣ ማርያም መግደላዊትና ሌላዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ ሄዱ።
2በድንገት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የጌታም መልአክ ከሰማይ ወርዶ ወደ መቃብሩ በመሄድ ድንጋዩን አንከባልሎ በላዩ ላይ ተቀመጠበት፤ 3መልኩ እንደ መብረቅ ብሩህ፣ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበር። 4ጠባቂዎቹ መልአኩን ከመፍራት የተነሣ ተንቀጠቀጡ፤ እንደ በድንም ሆኑ።
5መልአኩም ሴቶቹን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ ዐውቃለሁና፤ 6እርሱ በዚህ የለም፤ እንደ ተናገረው ተነሥቷል፤ ኑና ተኝቶበት የነበረውን ቦታ እዩ። 7አሁንም ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ፣ ‘ከሙታን ተነሥቷል፤ ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ በዚያ ታዩታላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው። እንግዲህ ነግሬአችኋለሁ!”
8ሴቶቹም በፍርሀትና በደስታ ተሞልተው ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር በፍጥነት እየሮጡ የመቃብሩን ስፍራ ትተው ሄዱ። 9ወዲያው ኢየሱስ አገኛቸውና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። 10ኢየሱስም፣ “አትፍሩ፤ ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ በዚያ ያዩኛል” አላቸው።
የጠባቂዎች ምስክርነት
11ሴቶቹ በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ከጠባቂዎቹ ጥቂቶቹ ወደ ከተማ በመሄድ የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩላቸው። 12የካህናት አለቆችም ከሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበው ተማከሩ፤ ለወታደሮቹ በቂ ገንዘብ በመስጠት 13እንዲህ አሏቸው፤ “ ‘ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት’ በሉ፤ 14ይህ ወሬ በገዥው ዘንድ ቢሰማ እንኳ፣ እኛ እናስረዳዋለን፤ ምንም ክፉ ነገር እንዳይደርስባችሁ እናደርጋለን።” 15ወታደሮቹም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ ታዘዙት አደረጉ። ይህም ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁዶች ዘንድ በሰፊው እንደ ተሠራጨ ነው።
ታላቁ ተልእኮ
16ከዚያም ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በገሊላ ወዳለው ኢየሱስ ወዳመለከታቸው ተራራ ሄዱ። 17ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ ጥቂቶች ግን ተጠራጠሩ። 18ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ 19ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ 20ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”
Currently Selected:
ማቴዎስ 28: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.