YouVersion Logo
Search Icon

ዘሌዋውያን 24

24
በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የሚቀርብ ዘይትና ኅብስት
24፥1-3 ተጓ ምብ – ዘፀ 27፥20-21
1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“መብራቶቹ ያለ ማቋረጥ እንዲያበሩ ከወይራ ተጨምቆ የተጠለለ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን እዘዛቸው። 3አሮንም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ መጋረጃ ውጭ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያሉትን መብራቶች ከምሽት እስከ ንጋት ያለ ማቋረጥ ያሰናዳቸው፤ ይህም ለትውልዶቻችሁ ሥርዐት ነው። 4በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በንጹሕ የወርቅ መቅረዝ ላይ ያሉት መብራቶች ያለ ማቋረጥ መሰናዳት አለባቸው።
5“የላመ ዱቄት ወስደህ ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ እያንዳንዱ ኅብስትም በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ#24፥5 4.5 ሊትር ገደማ ይሆናል መስፈሪያ ዱቄት ይጋገር። 6እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ረድፍ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ባለው የንጹሕ ወርቅ ጠረጴዛ ላይ አኑራቸው። 7ከኅብስቱ ጋር የመታሰቢያ ድርሻ ሆኖ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት እንዲሆን ንጹሕ ዕጣን በእያንዳንዱ ረድፍ ላይ አኑር። 8ኅብስቱ የእስራኤልን ሕዝብ ይወክል ዘንድ ዘወትር በየሰንበቱ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይደርደር፤ ይህም የዘላለም ቃል ኪዳን ነው። 9ኅብስቱ የአሮንና የልጆቹ ድርሻ ነው፤ በተቀደሰ ስፍራም ይበሉታል፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ድርሻቸው ነውና።”
እግዚአብሔርን መስደብ የሚያስከትለው ቅጣት
10እናቱ እስራኤላዊት፣ አባቱ ግብፃዊ የሆነ አንድ ሰው በእስራኤላውያን መካከል ወጣ፤ በሰፈርም ውስጥ ከአንድ እስራኤላዊ ጋር ተጣሉ። 11የእስራኤላዊቱ ልጅ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም በማቃለል ሰደበ፤ ስለዚህም ወደ ሙሴ አመጡት፤ የሰውየው እናት ስም ሰሎሚት ነበር፤ እርሷም ከዳን ወገን የተወለደው የደብራይ ልጅ ነበረች። 12የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፈቃድም ግልጽ እስኪሆንላቸው ድረስ በግዞት አኖሩት።
13 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 14“ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ አውጣው፤ ሲሳደብ የሰሙት ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ በድንጋይ ይውገረው። 15እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ማንም ሰው አምላኩን (ኤሎሂም) ቢሳደብ ኀጢአት ሠርቷልና ይጠየቅበታል። 16የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም የሚሳደብ ማንኛውም ሰው ይገደል፤ ማኅበሩ ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ከሰደበ ይገደል።
17“ ‘ሰውን ደብድቦ የገደለ ይገደል። 18የሌላውን ሰው እንስሳ ደብድቦ የገደለ ማንኛውም ሰው ያንኑ ዐይነት እንስሳ ይተካለት። 19ማንኛውም ሰው በባልንጀራው ላይ ጕዳት ቢያደርስ፣ የዚያው ዐይነት ጕዳት ይፈጸምበት፤ 20ይኸውም በስብራት ፈንታ ስብራት፣ በዐይን ፈንታ ዐይን፣ በጥርስ ፈንታ ጥርስ ማለት ነው። በሌላው ሰው ላይ ያደረሰው ጕዳት በእርሱም ላይ ይድረስበት፤ 21እንስሳ የገደለ ማንኛውም ሰው በገደለው ፈንታ ይተካ፤ ሰው የገደለ ግን ይገደል። 22ለመጻተኛው ሆነ ለአገር ተወላጅ አንድ ዐይነት ሕግ ይኑራችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።’ ”
23ሙሴም ይህን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ እነርሱም ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ ወስደው በድንጋይ ወገሩት፤ እስራኤላውያንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

Currently Selected:

ዘሌዋውያን 24: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ዘሌዋውያን 24