YouVersion Logo
Search Icon

ኢያሱ 1

1
እግዚአብሔር ኢያሱን አዘዘ
1 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከሞተ በኋላ፣ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ አለው፤ 2“እነሆ፤ ባሪያዬ ሙሴ ሞቷል፤ እንግዲህ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሡ፤ ለእስራኤላውያን ወደምሰጣቸው ምድር ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ። 3ለሙሴ በሰጠሁትም ተስፋ መሠረት፣ እግራችሁ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ እሰጣችኋለሁ። 4የርስታችሁ ዳርቻ ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስ፣ ከታላቁ ወንዝ ከኤፍራጥስ አንሥቶ፣ የኬጢያውያንን ምድር በሙሉ ይዞ፣ በምዕራብ በኩል እስከ ታላቁ ባሕር#1፥4 የሜድትራኒያን ባሕር ይደርሳል። 5በሕይወት በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ሁሉ ከአንተም ጋር እሆናለሁ፤ ከቶ አልጥልህም፤ አልተውህም።
6“ጽና፤ ለቀደሙት አባቶቻቸው እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር እንዲወርሱ፣ ይህን ሕዝብ የምትመራው አንተ ነህና በርታ። 7አይዞህ፤ ብቻ አንተ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ የሰጠህን ትእዛዝ ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቅ፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲሳካልህ፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። 8ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውን ሁሉ በጥንቃቄ እንድትፈጽመውም ቀንም ሆነ ሌት ከሐሳብህ አትለየው፤ ይህን ካደረግህ ያሰብኸው ይቃናል፤ ይሳካልም፤ 9በምትሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነውና አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና፤ አትፍራ፤ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?”
10ኢያሱም የሕዝቡን አለቆች እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ 11“ወደ ሰፈር ግቡ፤ ለሕዝቡም፣ ‘ስንቃችሁን አዘጋጁ፤ ከአሁን ጀምሮ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፣ እግዚአብሔር አምላካችሁ ርስት አድርጎ የሚሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ ትወርሳላችሁ’ በሏቸው።”
12ኢያሱ የሮቤልን ነገድ፣ የጋድን ነገድና የምናሴን ነገድ እኩሌታ እንዲህ አላቸው፤ 13የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንዲህ ሲል የሰጣችሁን ትእዛዝ አስቡ፤ ‘እግዚአብሔር አምላካችሁ ያሳርፋችኋል፤ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል።’ 14ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ እንዲሁም ከብቶቻችሁ ሙሴ በሰጣችሁ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባለው ምድር ይቈዩ፤ ነገር ግን ተዋጊዎቻችሁ ሁሉ፣ ከነሙሉ ትጥቃቸው፣ ከወንድሞቻችሁ ቀድመው ይሻገሩ፤ እናንተም ከወንድሞቻችሁ ጐን ተሰለፉ። 15ይህም፣ እግዚአብሔር እስኪያሳርፋቸውና ለእናንተም እንዳደረገው ሁሉ፣ እነርሱም እግዚአብሔር አምላካችሁ የሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ነው። ከዚህ በኋላ እናንተም ተመልሳችሁ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የሰጣችሁን፣ በፀሓይ መውጫ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ምድር ትወርሳላችሁ።”
16እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ያዘዝኸንን ሁሉ እናደርጋለን፤ ወደምትልከንም ሁሉ እንሄዳለን። 17ለሙሴ ሙሉ በሙሉ እንደ ታዘዝን ሁሉ፣ ለአንተም እንታዘዛለን፤ ብቻ እግዚአብሔር አምላክህ ከሙሴ ጋር እንደ ነበረ፣ አሁንም ከአንተ ጋር ይሁን። 18በትእዛዝህ ላይ የሚያምፅና ለቃልህ የማይታዘዝ ሁሉ ይገደል፤ ብቻ አንተ ጽና፤ አይዞህ፤ በርታ።”

Currently Selected:

ኢያሱ 1: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy