ኢዮብ 19
19
ኢዮብ
1ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤
2“ነፍሴን የምታስጨንቋት፣
በቃልስ የምትደቍሱኝ እስከ መቼ ነው?
3እነሆ፤ ዐሥር ጊዜ ዘለፋችሁኝ፤
ያለ ዕፍረትም በደላችሁኝ።
4በእውነት ተሳስቼ ከሆነ፣
ስሕተቱ የራሴ ጕዳይ ነው።
5ነገር ግን ራሳችሁን በእኔ ላይ ከፍ ብታደርጉ፣
መዋረዴንም እኔን ለመሞገት ብትጠቀሙበት፣
6እግዚአብሔር እንደ በደለኝ፣
በመረቡም እንደ ከበበኝ ዕወቁ።
7“ ‘ተበደልሁ’ ብዬ ብጮኽ ማንም አይመልስልኝም፤
ድምፄን ከፍ አድርጌ ባሰማም፣ ፍትሕ አላገኝም።
8እንዳላልፍ መንገዴን ዘግቷል፤
መሄጃዬንም በጨለማ ጋርዷል።
9ክብሬን ገፍፎኛል፤
ዘውዴንም ከራሴ ላይ ወስዷል።
10እስክወገድ ድረስ በሁሉ አቅጣጫ አፈራርሶኛል፤
ተስፋዬንም እንደ ዛፍ ነቅሎታል።
11ቍጣው በላዬ ነድዷል፤
እንደ ጠላቱም ቈጥሮኛል።
12ሰራዊቱ ገፍተው መጡ፤
በዙሪያዬ ምሽግ ሠሩ፤ ድንኳኔንም ከብበው ሰፈሩ።
13“ወንድሞቼን ከእኔ አርቋል፤
ከሚያውቁኝም ተገለልሁ።
14ዘመዶቼ ትተውኛል፤
ወዳጆቼም ረስተውኛል።
15የቤቴ እንግዶችና ሴት አገልጋዮቼ እንደ መጻተኛ ቈጠሩኝ፤
እንደ ባዕድም ተመለከቱኝ፤
16አገልጋዬን ብጣራ፣
በአንደበቴም ብለምነው፣ አይመልስልኝም።
17እስትንፋሴ ለሚስቴ እንኳ የሚያስጠላት ሆነ፤
የገዛ ወንድሞቼም ተጸየፉኝ።
18ሕፃናት እንኳ ይንቁኛል፤
ባዩኝም ቍጥር ያላግጡብኛል።
19የቅርብ ወዳጆቼ ሁሉ ተጸየፉኝ፤
የምወድዳቸውም በላዬ ተነሡ፤
20ቈዳና ዐጥንት ብቻ ሆኜ ቀረሁ፤
ድድ ብቻ ቀርቶልኝ አመለጥሁ።
21“ወዳጆቼ ሆይ፤ ራሩልኝ፤
የእግዚአብሔር እጅ መትታኛለችና ዕዘኑልኝ።
22እግዚአብሔር እንዳሳደደኝ ለምን ታሳድዱኛላችሁ?
አሁንም ሥጋዬ አልበቃችሁምን?
23“ምነው ቃሌ በተጻፈ ኖሮ!
በመጽሐፍም በታተመ!
24ምነው በብረትና በእርሳስ በተጻፈ ኖሮ!
በዐለትም ላይ በተቀረጸ!
25የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፣
በመጨረሻም በምድር ላይ እንደሚቆም ዐውቃለሁ።
26ቈዳዬ ቢጠፋም፣
ከሥጋዬ ብለይም፣ እግዚአብሔርን አየዋለሁ፤
27ሌላ ሳይሆን እኔው በገዛ ዐይኔ፣
እኔ ራሴ አየዋለሁ፤
ልቤ በውስጤ ምንኛ በጉጉት ዛለ!
28“ ‘የችግሩ መንሥኤ በውስጡ#19፥28 አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች፣ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕምና ቩልጌት፣ በእኔ ይላሉ። አለ፤
እኛ እንዴት እናሳድደዋለን?’ ብትሉ፣
29ቍጣ በሰይፍ መቀጣትን ያስከትላልና፣
ራሳችሁ ሰይፍን ፍሩ፤
በዚያን ጊዜ ፍርድ#19፥29 ወይም ሁሉን ቻዩን ታውቃላችሁ ማለት ነው። እንዳለ ታውቃላችሁ።”
Currently Selected:
ኢዮብ 19: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.