ኤርምያስ 16
16
የጥፋት ቀን
1 የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 2“በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይኑሩህ፤” 3በዚህች ምድር ስለሚወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፣ እንዲሁም ስለ እናቶቻቸው ስለ አባቶቻቸው እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ 4“በአደገኛ በሽታ ይሞታሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ አይቀበሩም፤ በምድርም ላይ እንደ ጕድፍ ይጣላሉ። በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል።”
5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “በረከቴን፣ ፍቅሬንና ምሕረቴን ከዚህ ሕዝብ አርቄአለሁና፤ ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፤ ታለቅስና ታዝንም ዘንድ አትሂድ” ይላል እግዚአብሔር። 6“ታላላቆችና ታናናሾች በዚህች ምድር ይሞታሉ፤ አይቀበሩም፤ አይለቀስላቸውም፤ ሰውነቱን የሚቧጥጥላቸው፣ ጠጕሩንም የሚላጭላቸው አይገኝም፤ 7ሐዘንተኞችን ለማጽናናት የዕዝን እንጀራ የሚያመጣ አይኖርም፤ አባትም ሆነ እናት የሞተባቸውንም ለማጽናናት መጠጥ የሚያቀርብ አይገኝም።
8“ከእነርሱ ጋር ተቀምጠህ ለመብላትና ለመጠጣት ድግስ ወዳለበት ቤት አትግባ፤ 9የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እነሆ፤ በዐይናችሁ ፊት፣ በዘመናችሁም የደስታና የሐሤት ድምፅ፣ የሙሽራውንና የሙሽራዪቱን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስወግዳለሁ።’
10“ይህን ሁሉ ለዚህ ሕዝብ በምትነግርበት ጊዜ ሰዎቹ፣ ‘እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ታላቅ ጥፋት በእኛ ላይ ለምን ዐወጀ? በደላችንስ ምንድን ነው? በአምላካችንስ በእግዚአብሔር ላይ የሠራነው ኀጢአት ምንድን ነው?’ ብለው ቢጠይቁህ፣ 11እንዲህ ትላቸዋለህ፤ ‘አባቶቻችሁ እኔን ስለ ተዉኝ ነው’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ሌሎችን አማልክት በመከተል፣ ስላገለገሏቸውና ስላመለኳቸው ነው፤ ትተውኝ ኰበለሉ፤ ሕጌንም አልጠበቁም። 12እናንተም ደግሞ ከአባቶቻችሁ የባሰ ክፉ ነገር አድርጋችኋል፤ እያንዳንዳችሁ እኔን በመታዘዝ ፈንታ የልባችሁን ክፋት ምን ያህል በእልኸኝነት እንደምትከተሉ ተመልከቱ። 13ስለዚህ ከዚህች ምድር አውጥቼ፣ እናንተም ሆነ አባቶቻችሁ ወደማታውቁት ምድር እጥላችኋለሁ፤ ምሕረትንም አላደርግላችሁምና በዚያ ሌሎችን አማልክት ቀንና ሌሊት ታገለግላላችሁ።’
14“ስለዚህ ሰዎች፣ ‘እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው ከእንግዲህ የማይምሉበት ዘመን ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤ 15“ነገር ግን፣ ‘እስራኤላውያንን ከሰሜን ምድርና እነርሱን ከበተነባቸው ከሌሎች አገሮች ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን!’ ይላሉ፤ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋቸው ምድር እመልሳቸዋለሁና።
16“አሁን ግን ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እልካለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “እነርሱም ያጠምዷቸዋል። ከዚያም በኋላ ብዙ ዐዳኞችን እሰድዳለሁ፤ እነርሱም ከየተራራው፣ ከየኰረብታው ሁሉ ከየዐለቱም ስንጣቂ ዐድነው ይይዟቸዋል። 17ዐይኔ በመንገዳቸው ሁሉ ላይ ነው፤ በፊቴ የተገለጡ ናቸው፤ ኀጢአታቸውም ከዐይኔ የተሰወረ አይደለም። 18ምድሬን በድን በሆኑ አስጸያፊ ጣዖቶቻቸው ስላረከሱ፣ ርስቴንም በአሳፋሪ ነገሮች ስለ ሞሉ፣ ላደረጉት በደልና ኀጢአት ዕጥፍ እከፍላቸዋለሁ።”
19ብርታቴና ምሽጌ፣
በመከራ ቀን መጠጊያዬ የሆንህ እግዚአብሔር ሆይ፤
አሕዛብ ከምድር ዳርቻ፣
ወደ አንተ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤
“አባቶቻችን ለአንዳች ነገር ያልረቧቸውን ከንቱ ጣዖቶች፣
የሐሰት አማልክትን ወረሱ።
20ሰዎች ለራሳቸው አማልክትን ያበጃሉን?
ያደርጉ ይሆናል፤ እንዲህ ዐይነቶቹ ግን አማልክት አይደሉም።”
21“ስለዚህ አስተምራቸዋለሁ፤
ኀይሌንና ታላቅነቴን፣
አሁን አስተምራቸዋለሁ፤
እነርሱም ስሜ እግዚአብሔር፣
እንደ ሆነ ያውቃሉ።
Currently Selected:
ኤርምያስ 16: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.