ኤርምያስ 15
15
1 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ሙሴና ሳሙኤል እንኳ በፊቴ ቢቆሙ፣ ልቤ ለዚህ ሕዝብ አይራራምና ከፊቴ አስወጣቸው፤ ይሂዱ! 2እነርሱም፣ ‘ወዴት እንሂድ?’ ቢሉህ፣ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ ‘ለሞት የተመደበ ወደ ሞት፣
ለሰይፍ የተመደበ ወደ ሰይፍ፣
ለራብ የተመደበ ወደ ራብ፣
ለምርኮ የተመደበ ወደ ምርኮ ይሄዳል።’
3“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አራት ዐይነት አጥፊዎችን እሰድድባቸዋለሁ፤ እነዚህም፣ ለመግደል ሰይፍ፣ ለመጐተት ውሾች፣ እንዲሁም ጠራርጎ ለመብላትና ለማጥፋት የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት ናቸው። 4የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ካደረገው በደል የተነሣ፣ ለምድር ነገሥታት ሁሉ መሰቀቂያ አደርጋቸዋለሁ።’
5“ኢየሩሳሌም ሆይ፤ የሚራራልሽ ማን ነው?
ማንስ ያለቅስልሻል?
ደኅንነትሽንስ ማን ጐራ ብሎ ይጠይቃል?
6እኔን ጥለሽኛል” ይላል እግዚአብሔር፤
“ወደ ኋላም እያፈገፈግሽ ነው፤
ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤ አጠፋሻለሁም፤
ከእንግዲህም አልራራልሽም።
7በአገሪቱ የከተማ ደጆች፣
በመንሽ እበትናቸዋለሁ፤
ከመንገዳቸው አልተመለሱምና፣
ሕዝቤን በሐዘን እመታለሁ፤
ጥፋትም አመጣባቸዋለሁ፤
8የመበለቶቻቸውን ቍጥር፣
ከባሕር አሸዋ ይልቅ አበዛለሁ፤
የጐበዛዝት እናቶች በሆኑትም ላይ፣
አጥፊውን በቀትር አመጣባቸዋለሁ።
ሽብርንና ድንጋጤን፣
በድንገት አወርድባቸዋለሁ።
9የሰባቶቹ እናት ትዝለፈለፋለች፤
ትንፋሿም ይጠፋል፤
ገና ቀን ሳለ ፀሓይዋ ትጠልቃለች፤
እርሷም ታፍራለች፤ ትዋረዳለችም፤
የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት፣
ለሰይፍ እዳርጋቸዋለሁ፤”
ይላል እግዚአብሔር።
10ወይኔ እናቴ! ለምድር ሁሉ፣
የጭቅጭቅና የክርክር ሰው የሆንሁትን ምነው ወለድሽ!
ለማንም አላበደርሁም፤ ከማንም አልተበደርሁም፤
ነገር ግን ሰው ሁሉ ይረግመኛል።
11 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤
“በርግጥ ለበጎ ዐላማ እታደግሃለሁ፤
በመከራና በጭንቅ ጊዜም፣
ጠላቶችህ ደጅ እንዲጠኑህ በእውነት አደርጋለሁ።
12“ሰው ብረትን፣ ከሰሜን የመጣን ብረት፣
ነሐስንስ መስበር ይችላልን?
13በመላ አገርህ፣
ስላለው ኀጢአትህ ሁሉ፣
ሀብትና ንብረትህን፣
ያለ ዋጋ አሳልፌ ለምርኮ እሰጣለሁ።
14ቍጣዬ በላያችሁ፣
የሚነድድ እሳት ትጭራለችና፣
በማታውቀው አገር፣
ለጠላቶችህ#15፥14 አንዳንድ የዕብራይስጥ ጽሑፎች፣ ሰብዓ ሊቃናትና ሱርሰት ጽሑፎች ጠላቶችህ እንዲወስዱህ አደርጋለሁ ይላሉ። ባሪያ አደርግሃለሁ።”
15 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ታውቃለህ፤
እንግዲህ አስበኝ፤ ጐብኘኝም፤
አሳዳጆቼን ተበቀልልኝ።
ታጋሽ እንደ መሆንህ አታጥፋኝ፤
ባንተ ምክንያት የሚደርስብኝን ነቀፋ ዐስብ።
16ቃልህ በተገኘ ጊዜ በላሁት፤
የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤
በስምህ ተጠርቻለሁና፣
ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነልኝ።
17ፈንጠዝያ ከሚያደርጉት ጋር አልተቀመጥሁም፤
ከእነርሱም ጋር አልፈነጨሁም፤
እጅህ በላዬ ስለ ነበር፣ በቍጣህ ስለ ሞላኸኝ፣
ለብቻዬ ተቀመጥሁ።
18ሕመሜ ለምን ጸናብኝ?
ቍስሌስ ለምን በረታብኝ? ለምንስ የማይፈወስ ሆነ?
እንደሚያታልል ወንዝ፣
እንደሚያሳስት ምንጭ ትሆንብኛለህን?
19ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ብትመለስ፣ መልሼ አቆምሃለሁ፤
ታገለግለኛለህም፤
የከበረውን ከማይረባው ለይተህ ብትናገር፣
አፍ ትሆነኛለህ፤
እነርሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ እንጂ፣
አንተ ወደ እነርሱ አትመለስም፤
20ለዚህ ሕዝብ የናስ ቅጥር፣ የተመሸገ
የናስ ቅጥር አደርግሃለሁ፤
ልታደግህና፣ ላድንህም፣
እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፤
ቢዋጉህም እንኳ፣
ሊያሸንፉህ አይችሉም፤”
ይላል እግዚአብሔር።
21“ከክፉዎች እጅ እቤዥሃለሁ፤
ከጨካኞችም ጭምደዳ እታደግሃለሁ።”
Currently Selected:
ኤርምያስ 15: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.