YouVersion Logo
Search Icon

ኤርምያስ 1

1
1የኬልቅያስ ልጅ፣ ኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ አባቱ በብንያም አገር በዓናቶት ከሚገኙት ካህናት አንዱ ነበረ። 2የእግዚአብሔር ቃል የይሁዳ ንጉሥ፣ የአሞን ልጅ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ወደ ኤርምያስ መጣ፤ 3ደግሞም በይሁዳ ንጉሥ፣ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ንግሠ ዘመን፤ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ፣ በኢዮስያስ ልጅ በሴዴቅያስ ንግሠ ዘመን፤ እስከ ዐሥራ አንደኛው ዓመት መጨረሻ ድረስ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ተማርኮ እስከ ሄደበት እስከ አምስተኛው ወር ድረስ ወደ እርሱ ይመጣ ነበር።
የኤርምያስ መጠራት
4 የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፤
5“በማሕፀን ሳልሠራህ ዐወቅሁህ፤
ከመወለድህ በፊት ለየሁህ፤#1፥5 ወይም መረጥሁህ
ለሕዝቦችም ነቢይ እንድትሆን ሾምሁህ።”
6እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝና” አልሁ።
7 እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፤ “ ‘ገና ሕፃን ልጅ ነኝ’ አትበል፤ ወደምልክህ ሁሉ ሄደህ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ትናገራለህ፤ 8እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራቸው” ይላል እግዚአብሔር
9 እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰና እንዲህ አለኝ፤ “እነሆ፤ ቃሌን በአፍህ አኑሬአለሁ፤ 10እንግዲህ፣ እንድትነቅልና እንድታፈርስ፣ እንድታጠፋና እንድትገለብጥ፣ እንድታንጽና እንድትተክል በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ ሾምሁህ።”
11 የእግዚአብሔር ቃል፣ “ኤርምያስ ሆይ፣ ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ።
እኔም፣ “የለውዝ በትር አያለሁ” አልሁ።
12 እግዚአብሔርም፣ “ትክክል አይተሃል፤ ቃሌን እፈጽመው ዘንድ እተጋለሁና”#1፥12 እተጋለሁ ለሚለው የዕብራይስጡ አነባበብ የለውዝ በትር ከሚለው ጋር ይመሳሰላል። አለኝ።
13ዳግመኛም የእግዚአብሔር ቃል፣ “ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ።
እኔም፣ “አንድ የሚፈላ ማሰሮ አያለሁ፤ አፉም ከሰሜን ወደዚህ ያዘነበለ ነው” አልሁ።
14 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ከሰሜን በምድሪቱ በሚኖሩ ሁሉ ላይ ድንገት መዓት ይወርድባቸዋል። 15እነሆ፤ የሰሜን መንግሥታትን ሕዝቦች ሁሉ እጠራለሁ” ይላል እግዚአብሔር
“ንጉሦቻቸው ይመጣሉ፤
ዙፋናቸውን በኢየሩሳሌም መግቢያ በሮች፣
በቅጥሮቿ ዙሪያ ሁሉ፣
በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ይዘረጋሉ።
16እኔን በመተው ክፋት ስለ ሠሩ፣
ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑ፣
እጆቻቸው የሠሯቸውን ስላመለኩ፣
በሕዝቤ ላይ ፍርድን ዐውጄአለሁ።
17“አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፤ ተነሥተህም ያዘዝሁን ሁሉ ንገራቸው፤ አትፍራቸውም፤ አለዚያ በፊታቸው አስፈራሃለሁ። 18እነሆ፤ ዛሬ በመላዪቱ ምድር ላይ አስነሣሃለሁ፤ ይኸውም የይሁዳን ነገሥታት፣ አለቆቿን፣ ካህናቷንና የምድሪቱን ሕዝብ ሁሉ መቋቋም እንድትችል የተመሸገ ከተማ፣ የብረት ምሰሶና የናስ ቅጥር አድርጌሃለሁ። 19ይዋጉሃል፤ ዳሩ ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም” ይላል እግዚአብሔር

Currently Selected:

ኤርምያስ 1: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in