መሳፍንት 17
17
ሚካ ያሠራቸው ጣዖታት
1ሚካ የተባለ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር የሚኖር ሰው ነበር። 2እናቱን፣ “አንድ ሺሕ አንድ መቶ ሰቅል#17፥2 13 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር ተሰርቆብሽ፣ የሰረቀውን ሰው ስትራገሚ ሰምቼሽ ነበር፤ ብሩ ከእኔ ዘንድ ይገኛል፤ የወሰድሁት እኔ ነኝ” አላት።
ከዚያም እናቱ፣ “ልጄ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለችው።
3አንድ ሺሕ አንድ መቶውን ሰቅል ብር በመለሰላት ጊዜ እናቱ፣ “ብሬን የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት ለማበጀት ስለ ልጄ ለእግዚአብሔር እቀድሰዋለሁ፤ አሁንም ለአንተው መልሼ እሰጥሃለሁ” አለችው።
4ስለዚህ ብሩን ለእናቱ መለሰላት፤ እናቱም ከላዩ ሁለት መቶ ጥሬ#17፥4 17፥4 2.3 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር ወስዳ ለብር አንጥረኛ ሰጠች፤ አንጥረኛውም የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት አደረገው፤ ምስሎቹም በሚካ ቤት ተቀመጡ።
5ሚካ የተባለው ይህ ሰው የአምልኮ ስፍራ ነበረው፤ አንድ ኤፉድና ተራፊም ሠርቶ ከልጆቹ አንዱን ካህን ሆኖ እንዲያገለግለው አደረገ። 6በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ እያንዳንዱ ሰው ለራሱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር። 7በይሁዳ ምድር፣ በይሁዳ ነገድ መካከል በቤተ ልሔም የሚኖር አንድ ሌዋዊ ወጣት ነበር። 8ይህም ሰው ሌላ መኖሪያ ስፍራ ለመፈለግ ከተማዪቱን ለቆ ሄደ። በሚጓዝበትም#17፥8 ወይም የዕለት ምግባሩን እያከናወነ ሳለ ጊዜ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር ወዳለው ወደ ሚካ ቤት መጣ።
9ሚካም፣ “የየት አገር ሰው ነህ?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም፣ “እኔ በይሁዳ ምድር ከምትገኝ ከቤተ ልሔም የመጣሁ ሌዋዊ ነኝ፤ መኖሪያ ስፍራ እፈልጋለሁ” አለው።
10ሚካም፣ “እንግዲያውስ አብረኸኝ ተቀመጥ፤ አባትም ካህንም ሁነኝ፤ እኔም በዓመት ዐሥር ሰቅል#17፥10 110 ግራም ያህል ነው። ብር እንዲሁም ልብስና ምግብ እሰጥሃለሁ” አለው። 11ስለዚህ ሌዋዊው አብሮት ለመኖር ተስማማ፤ ወጣቱም ለሚካ ከልጆቹ እንደ አንዱ ሆነለት። 12ሚካም ሌዋዊውን ካህን አድርጎ አስቀመጠው፤ ወጣቱም ካህኑ ሆነ፤ በቤቱም ኖረ። 13ሚካም፤ “ይህ ሌዋዊ ካህን ለሆነልኝ፣ እግዚአብሔር በጎ ነገር እንደሚያደርግልኝ አሁን ተረዳሁ” አለ።
Currently Selected:
መሳፍንት 17: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.