YouVersion Logo
Search Icon

መሳፍንት 10

10
ቶላ
1ከአቤሜሌክ በኋላ ከይሳኮር ነገድ የሆነ የዱዲ ልጅ፣ የፎሖ ልጅ ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፤ እርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር ሳምር በምትባል መንደር ይኖር ነበር። 2ቶላ በእስራኤል ላይ ሃያ ሦስት ዓመት በፈራጅነት ከተቀመጠ በኋላ ሞተ፤ በሳምርም ተቀበረ።
ኢያዕር
3ከቶላ ቀጥሎ ገለዓዳዊው ኢያዕር ተነሣ፤ እርሱም በእስራኤል ላይ ሃያ ሁለት ዓመት በፈራጅነት#10፥3 በዚህና በቍጥር 3 ላይ በትውፊት መሳፍንት ይባላል። ተቀመጠ። 4ኢያዕር በሠላሳ አህዮች የሚጋልቡ ሠላሳ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ልጆቹም እስከ ዛሬ ድረስ የኢያዕር መንደሮች ተብለው የሚጠሩ ሠላሳ ከተሞች በገለዓድ ምድር ነበሯቸው። 5ኢያዕር ሞተ፤ በቃሞንም ተቀበረ።
ዮፍታሔ
6እስራኤላውያን እንደ ገና በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ በኣልንና አስታሮትን እንዲሁም የሶሪያን፣ የሲዶናን፣ የሞዓብን፣ የአሞንንና የፍልስጥኤማውያንን አማልክት አመለኩ፤ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ስለ ተዉና ስላላገለገሉት፣ 7ተቈጣቸው፤ በፍልስጥኤማውያንና በአሞናውያን እጅ ሸጣቸው፤ 8እነርሱም በዚያን ዓመት ሰበሯቸው፤ አደቀቋቸውም፤ እስራኤላውያንን ሁሉ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባለው በገለዓድ ምድር፣ 9በአሞራውያን አገር ዐሥራ ስምንት ዓመት እንዲሁም አሞናውያን ይሁዳን፣ ብንያምንና የኤፍሬምን ቤት ለመውጋት ዮርዳኖስን ስለ ተሻገሩ እስራኤላውያን እጅግ ተጨነቁ። 10ከዚያም እስራኤላውያን፣ “አንተን አምላካችንን በመተው የበኣልን አማልክት በማምለካችን አንተን በድለናል” ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
11 እግዚአብሔርም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ግብፃውያን፣ አሞራውያን፣ አሞናውያን፣ ፍልስጥኤማውያን፣ 12ሲዶናውያን፣ አማሌቃውያንና ማዖናውያን#10፥12 አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ምድያማውያን ይላሉ። አሠቃዩአችሁ፤ እናንተም እንድረዳችሁ ወደ እኔ ጮኻችሁ፤ ታዲያ እኔ ከእጃቸው አላዳንኋችሁምን? 13እናንተ ግን እኔን ትታችሁ ሌሎች አማልክትን አመለካችሁ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ አላድናችሁም፤ 14ሂዱና ወደ መረጣችኋቸው አማልክት ጩኹ፤ መከራ በሚያገኛችሁ ጊዜ እስቲ ያድኗችሁ።”
15እስራኤላውያንም እግዚአብሔርን፣ “ኀጢአት ሠርተናል፤ መልካም መስሎ የታየህን አድርግብን፤ እባክህን የዛሬን ብቻ አድነን” አሉት። 16ከዚያም በመካከላቸው ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወገዱ፤ እግዚአብሔርንም አመለኩ፤ እግዚአብሔርም እስራኤል ስትጐሳቈል ዝም ብሎ ማየት አልቻለም።
17አሞናውያን ለጦርነት ዝግጁ ሆነው በገለዓድ በሰፈሩ ጊዜ፣ እስራኤላውያንም እንደዚሁ ተሰብስበው በምጽጳ ሰፈሩ። 18የገለዓድ ሕዝብ አለቆችም እርስ በእርሳቸው፣ “በአሞናውያን ላይ ጦርነቱን የሚጀምር ሰው በገለዓድ ነዋሪዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሆናል” ተባባሉ።

Currently Selected:

መሳፍንት 10: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for መሳፍንት 10