ኢሳይያስ 7
7
የዐማኑኤል ምልክትነት
1የዖዝያን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን፣ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ነገር ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም።
2ለዳዊት ቤት፣ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፣ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ።
3 እግዚአብሔርም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፤ “አንተና ልጅህ ሸአር ያሹብ#7፥3 ሸአር ያሹብ ማለት፣ ቅሬታዎች ይመለሳሉ ማለት ነው። አካዝን ለመገናኘት ወደ ልብስ ዐጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤ 4እንዲህም በለው፤ ‘ተጠንቀቅ፤ ተረጋጋ፤ አትፍራ፤ በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱት በሁለቱ የዕንጨት ጕማጆች፣ በሶርያና በንጉሥዋ በረአሶን እንዲሁም በሮሜልዩ ልጅ ቍጣ አትሸበር። 5ሶርያ ኤፍሬምና፣ የሮሜልዩ ልጅ ሊያጠፉህ እንዲህ ብለው ተማከሩ፤ 6“ይሁዳን እንውረር፤ እንበታትነው፤ ተከፋፍለንም እንግዛው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥባት።” 7ጌታ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤
“ ‘ይህ ምክራቸው አይፈጸምም፤
ከቶም አይደረግም፤
8የሶርያ ራስ ደማስቆ፣
የደማስቆ ራስ ረአሶን ነውና፤
በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ፣
የኤፍሬም ሕዝብ ይበታተናል፤ ሕዝብ መሆኑም ይቀራል።
9የኤፍሬም ራስ ሰማርያ፣
የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው።
እንግዲህ በእምነታችሁ ካልጸናችሁ፣
ፈጽሞ መቆም አትችሉም።’ ”
10እንደ ገናም እግዚአብሔር አካዝን እንዲህ አለው፤ 11“ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ ምልክት እንዲሰጥህ ከእግዚአብሔር ከአምላክህ ለምን።”
12አካዝ ግን፣ “አልለምንም፣ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” አለ።
13ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ፤ የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን? 14ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል#7፥14 ዐማኑኤል ማለት፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው። ብላ ትጠራዋለች። 15ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል። 16ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል። 17ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፣ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው።”
18በዚያን ቀን እግዚአብሔር ራቅ ካሉት ከግብፅ ወንዞች ዝንቦችን፣ ከአሦርም ምድር ንቦችን በፉጨት ይጠራል። 19እነርሱም በሙሉ መጥተው፣ በየበረሓው ሸለቆ፣ በየዐለቱ ንቃቃት፣ በየእሾኹ ቍጥቋጦና በየውሃው ጕድጓድ ሁሉ ይሰፍራሉ። 20በዚያን ቀን፣ እግዚአብሔር ከወንዝ#7፥20 የኤፍራጥስ ወንዝ ነው። ማዶ በተከራየው ምላጭ፣ ማለትም በአሦር ንጉሥ፣ የራስና የእግር ጠጕራችሁን እንዲሁም ጢማችሁን ይላጫል። 21በዚያን ቀን፣ አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በግ ብቻ ይተርፈዋል። 22ከሚሰጡትም የተትረፈረፈ ወተት ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱም የቀሩ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላሉ። 23በዚያን ቀን ሺሕ ሰቅል#7፥23 11.5 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር የሚያወጣ አንድ ሺሕ የወይን ተክል የነበረበት ቦታ ሁሉ፣ ኵርንችትና እሾኽ ብቻ ይሆናል። 24ምድሪቱ በኵርንችትና በእሾኽ ስለምትሸፈን፣ ሰዎች ወደዚያ የሚገቡት ቀስትና ፍላጻ ይዘው ነው፤ 25ኵርንችትና እሾኹን በመፍራት ከዚህ በፊት በመቈፈሪያ ተቈፍረው ወደ ነበሩት ወደ እነዚያ ኰረብታዎች ሁሉ ከእንግዲህ አትሄድም፤ ነገር ግን የከብቶች መሰማሪያና የበጎች መፈንጫ ቦታ ይሆናሉ።
Currently Selected:
ኢሳይያስ 7: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.