ኢሳይያስ 53:4-12
ኢሳይያስ 53:4-12 NASV
በርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ እኛ ግን በእግዚአብሔር እንደ ተመታ፣ እንደ ተቀሠፈ፣ እንደ ተሠቃየም ቈጠርነው። ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጐድን፤ እግዚአብሔርም፣ የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ ጫነው። ተጨነቀ፤ ተሠቃየም፤ ነገር ግን አፉን አልከፈተም፤ እንደ ጠቦትም ለዕርድ ተነዳ፤ በሸላቾች ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኀጢአት ተመትቶ፣ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ፣ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? በአፉ ተንኰል ሳይገኝበት፣ ምንም ወንጀል ሳይሠራ፣ አሟሟቱ ከክፉዎች፣ መቃብሩም ከባለጠጎች ጋር ሆነ። መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤ እግዚአብሔር ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገውም እንኳ፣ ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል፤ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ሥቃይ በኋላ፣ የሕይወት ብርሃን ያያል፤ ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬ በዕውቀቱ ብዙዎቹን ያጸድቃል፤ መተላለፋቸውንም ይሸከማል። ስለዚህ ድርሻውን ከታላላቆች ጋር እሰጠዋለሁ፤ ምርኮውን ከኀያላን ጋር ይካፈላል፤ እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠቱ፣ ከክፉ አድራጊዎችም ጋር በመቈጠሩ፣ የብዙዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤ ስለ ዐመፀኞችም ማለደ።