YouVersion Logo
Search Icon

ኢሳይያስ 25

25
ምስጋና ለእግዚአብሔር
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤
ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም አወድሳለሁ፤
አስቀድሞ የታሰበውን፣
ድንቅ ነገር፣
በፍጹም ታማኝነት አድርገሃልና።
2ከተማዪቱን የድንጋይ ክምር አድርገሃታል፤
የተመሸገችውንም ከተማ አፈራርሰሃታል፤
የተመሸገችው የባዕድ ከተማ ከእንግዲህ አትኖርም፤
ተመልሳም አትሠራም።
3ስለዚህ ብርቱ ሕዝቦች ያከብሩሃል፤
የጨካኝ አሕዛብ ከተሞችም ይፈሩሃል።
4ለድኻ መጠጊያ፣
በጭንቅ ጊዜ ለችግረኛ መጠለያ፣
ከማዕበል መሸሸጊያ፣
ከፀሓይ ትኵሳትም ጥላ ሆነሃል።
የጨካኞች እስትንፋስ፣
ከግድግዳ ጋር እንደሚላጋ ማዕበል ነውና፤
5እንደ ምድረ በዳም ትኵሳት ነው።
የባዕድን ጩኸት እረጭ ታደርጋለህ፤
ትኵሳት በደመና ጥላ እንደሚበርድ፣
የጨካኞችም ዝማሬም እንዲሁ ጸጥ ይላል።
6የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በዚህ ተራራ ላይ፣
ለሕዝብ ሁሉ ታላቅ የምግብ ግብዣ፣
የበሰለ የወይን ጠጅ ድግስ፣
ማለፊያ ጮማና ምርጥ የወይን ጠጅ ያዘጋጃል።
7በዚህም ተራራ ላይ፣
በሕዝብ ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፣
በመንግሥታት ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል፤
8ሞትንም ለዘላለም ይውጣል።
ጌታ እግዚአብሔር
ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤
የሕዝቡንም ውርደት
ከምድር ሁሉ ያስወግዳል፤
እግዚአብሔር ተናግሯልና።
9በዚያን ቀን እንዲህ ይባላል፤
“እነሆ፤ አምላካችን ይህ ነው፤
በእርሱ ታመንን፤ እርሱም አዳነን፤
እግዚአብሔር ይህ ነው፤ በእርሱ ታመንን፤
በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ።”
10 የእግዚአብሔር እጅ በዚህ ተራራ ላይ ያርፋል፤
ነገር ግን ጭድ ከጭቃ ጋር እንደሚረገጥ፣
ሞዓብም እንዲሁ ይረገጣል።
11ዋናተኛ ሲዋኝ እጁን እንደሚዘረጋ፣
በውስጡ ሆነው እጃቸውን ይዘረጋሉ፤
ጌታ በእጃቸው ተንኰል ሳይታለል፣
ትዕቢታቸውን ያዋርዳል።
12ከፍ ብሎ የተመሸገውን ቅጥርህን ዝቅ ያደርገዋል፤
ወደ ታች ያወርደዋል፤
ወደ ምድር አውርዶም
ትቢያ ላይ ይጥለዋል።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 25: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in