YouVersion Logo
Search Icon

ዘፍጥረት 49

49
ያዕቆብ ልጆቹን ባረከ
49፥1-28 ተጓ ምብ – ዘዳ 33፥1-29
1ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልጆቹን ሁሉ አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በኋለኛው ዘመን ምን እንደሚደርስባችሁ እነግራችሁ ዘንድ ተሰብሰቡ፤
2“እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤
ተሰብሰቡና ስሙ፤
አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ፤
3“ሮቤል፣ አንተ የበኵር ልጄ ነህ፤
ኀይሌና የጕብዝናዬም መጀመሪያ፤
በክብር ትልቃለህ፤ በኀይልም
ትበልጣለህ።
4እንደ ውሃ የዋለልህ ነህና እልቅና
አይኖርህም፤
የአባትህን መኝታ ደፍረሃል፤
ምንጣፌንም አርክሰሃል።
5“ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች፣
ሰይፎቻቸው#49፥5 በዕብራይስጥ የዚህ ቃል ትርጕም አይታወቅም። የዐመፅ መሣሪያዎች ናቸው።
6ወደ ሸንጓቸው አልግባ፤
ጉባኤያቸው ውስጥ አልገኝ፤
በቍጣ ተነሣሥተው ሰዎችን ገድለዋል፤
የበሬዎችንም ቋንጃ እንዳሻቸው ቈራርጠዋል።
7እጅግ አስፈሪ የሆነ ቍጣቸው፣
ጭከና የተሞላ ንዴታቸው የተረገመ ይሁን፤
በያዕቆብ እበትናቸዋለሁ፤
በመላው እስራኤልም አሠራጫቸዋለሁ።
8“ይሁዳ፣#49፥8 ይሁዳ የሚለው ቃል ውዳሴ የሚል ትርጕም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ሲሆን፣ ከዚሁ ቃል ጋር አንድ ዐይነት ድምፅ አለው። ወንድሞችህ ይወድሱሃል፤
እጅህም የጠላቶችህን ዐንገት ዐንቆ ይይዛል፤
የአባትህ ልጆች በፊትህ ተደፍተው ይሰግዱልሃል።
9አንተ የአንበሳ ደቦል ይሁዳ፤
ከዐደንህ የምትመለስ ልጄ፣
እንደ አንበሳ ያደፍጣል፤ በምድርም ላይ ይተኛል፤
እንደ እንስት አንበሳም ያደባል፤
ታዲያ ማን ሊቀሰቅሰው ይደፍራል?
10በትረ መንግሥት ከይሁዳ እጅ አይወጣም፤
የገዥነት ምርኵዝም ከእግሮቹ መካከል።
ገዥነት የሚገባው እስኪመጣ ድረስ፣#49፥10 ወይም ሴሎ እስኪመጣ ድረስ ወይም ክብር የሚገባው እስኪመጣ ድረስ
ሕዝቦች ሁሉ ይታዘዙታል።
11አህያውን በወይን ግንድ፣
ውርንጫውንም በምርጡ የወይን ሐረግ
ቅርንጫፍ ላይ ያስራል፤
ልብሱን በወይን ጠጅ፣
መጐናጸፊያውንም በወይን ጭማቂ ያጥባል።
12ዐይኖቹ ከወይን ጠጅ የቀሉ፣
ጥርሶቹም ከወተት ይልቅ የነጡ ይሆናሉ።
13“ዛብሎን፣ በባሕር ዳር ይኖራል፤
የመርከቦች መጠጊያም ይሆናል፤
ወሰኑም እስከ ሲዶና ይደርሳል።
14“ይሳኮር፣ በጭነት#49፥14 የመስክ ላይ እሳት መካከል የሚተኛ
ዐጥንተ ብርቱ አህያ ነው።
15ማረፊያ ቦታው መልካም፣
ምድሪቱም አስደሳች መሆኗን ሲያይ፣
ትከሻውን ለሸክም ያመቻቻል፤
ተገድዶም ያገለግላል።
16“ዳን፣#49፥16 ዳን ማለት ፍትሕ ይሰጣል ማለት ነው። ከእስራኤል ነገዶች እንደ አንዱ ሆኖ፣
በራሱ ሕዝብ ላይ ይፈርዳል።
17ዳን የመንገድ ዳር እባብ፣
የመተላለፊያም መንገድ እፉኝት ነው፤
ጋላቢው የኋሊት እንዲወድቅ፣
የፈረሱን ሰኰና ይነክሳል።
18እግዚአብሔር ሆይ (ያህዌ)፤ ማዳንህን እጠባበቃለሁ።
19“ጋድን#49፥19 ጋድ ማለት ማጥቃት እንዲሁም ወራሪ ሰራዊት ማለት ነው። ወራሪዎች አደጋ ይጥሉበታል፤
እርሱ ግን ዱካቸውን ተከታትሎ ብድሩን ይመልሳል።
20“አሴር ማእደ ሰፊ ይሆናል፤
ለነገሥታትም የሚስማማ ምግብ ያቀርባል።
21“ንፍታሌም ነጻ እንደ ተለቀቀች፣
የሚያማምሩም ግልገሎች#49፥21 ወይም ነጻ፤ ውብ ቃሎችን የሚናገር
እንደምትወልድ ሚዳቋ ነው።
22“ዮሴፍ፤ ፍሬያማ የወይን ተክል፣
በምንጭ ዳር የተተከለ ወይን ነው።
ሐረጎቹ ቅጥርን ያለብሳሉ።#49፥22 ወይም ዮሴፍ የዱር የፈረስ ግልገል፣ በምንጭ ዳር ያለ የፈረስ ግልገል፣ በባለ ዕርከን ኰረብታ ላይ የዱር አህያ ነው
23ቀስተኞች በጭካኔ አጠቁት፤
በጥላቻም ነደፉት።
24ነገር ግን በያዕቆብ ኀያል አምላክ ክንድ፣#49፥23-24 ወይም ቀስተኞች ያጠቃሉ… ያስፈነጥራሉ… ይኖራሉ… ይቈያሉ
እረኛው በሆነው በእስራኤል ዐለት፣ ቀስቱ ጸና፤
ጠንካራ ክንዱም ቀለጠፈ።
25አንተን በሚረዳህ በአባትህ አምላክ፣
በሚባርክህ፣ ሁሉን ማድረግ በሚችል አምላክ፣#49፥25 ዕብራይስጡ ሻዳይ ይለዋል
ከላይ ከሰማይ በሚገኝ ረድኤት፣
ከምድር ጥልቅ በሚገኝ በረከት፣
ከማሕፀንና ከጡት በሚገኝ ምርቃት ይባርክሃል።
26ከጥንት ተራሮች በረከት፣
ከዘላለም ኰረብቶች ምርቃት ይልቅ፣
የአባትህ በረከት ይበልጣል።#49፥26 …ከአያት ቅድማያቶቼ… ታላቅ ነው
ይህ ሁሉ በዮሴፍ ራስ ላይ ይውረድ፤
በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም ግንባር ላይ ይረፍ።#49፥26 ወይም ከ… የተለየ
27“ብንያም፣ ነጣቂ ተኵላ ነው፤
ያደነውን ማለዳ ይበላል፤
የማረከውን ማታ ይከፋፈላል።”
28እነዚህ ሁሉ ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው። ይህም እያንዳንዳቸውን ተገቢ በሆነው በረከት አባታቸው ሲባርካቸው የተናገረው ቃል ነው።
የያዕቆብ መሞት
29ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ወገኖቼ የምሰበሰብበት ጊዜ ደርሷል፤ በኬጢያዊው በኤፍሮን ዕርሻ ውስጥ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ዘንድ ቅበሩኝ፤ 30ይህ በከነዓን ምድር፣ በመምሬ አጠገብ፣ በማክፌላ ዕርሻ ውስጥ ያለው ዋሻ፣ የመቃብር ቦታ እንዲሆን አብርሃም ከኬጢያዊው ኤፍሮን ላይ ከነዕርሻ ቦታው የገዛው ነው። 31በዚያ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ተቀብረዋል፤ በዚያ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ተቀብረዋል፤ 32እኔም ልያን የቀበርኋት እዚያው ነው። ዕርሻውና ዋሻው የተገዙት ከኬጢያውያን#49፥32 ወይም ከኬጢ ልጆች ላይ ነው።”
33ያዕቆብ እነዚህን ቃላት ለልጆቹ ተናግሮ እንዳበቃ፣ እግሮቹን በዐልጋው ላይ ሰብስቦ፣ የመጨረሻ ትንፋሹን ተነፈሰ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።

Currently Selected:

ዘፍጥረት 49: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in