YouVersion Logo
Search Icon

ዘፍጥረት 17

17
የግዝረት ኪዳን
1አብራም ዕድሜው 99 ዓመት በሆነ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ#17፥1 ሁሉን የሚገዛ ማለት ነው። ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፤ ነቀፋም አይኑርብህ፤ 2በእኔና በአንተ መካከል የተመሠረተውን ኪዳን አጸናለሁ፤ ዘርህንም እጅግ አበዛለሁ።”
3አብራም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ 4“እነሆ፤ የምገባልህ ኪዳን ይህ ነው፤ የብዙ ሕዝቦች አባት ትሆናለህ። 5ከእንግዲህ ወዲያ ስምህ አብራም#17፥5 አብራም ማለት የከበረ አባት ማለት ነው። መባሉ ቀርቶ አብርሃም ይሆናል፤ የብዙ ሕዝቦች አባት አድርጌሃለሁና። 6ዘርህን እጅግ አበዛለሁ፤ ብዙ ሕዝብም አደርግሃለሁ፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። 7በእኔና በአንተ፣ ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋራ ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ በዚህም የአንተና ከአንተም በኋላ የዘርህ አምላክ እሆናለሁ። 8ይህችን አሁን በእንግድነት የምትኖርባትን የከነዓንን ምድር በሙሉ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ ለዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ።”
9ከዚያም እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በአንተም በኩል፣ አንተና ከአንተ በኋላ የሚመጣው ዘርህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ኪዳኔን ትጠብቃላችሁ። 10አንተና ከአንተም በኋላ የሚመጣው ዘርህ የምትጠብቁት ኪዳን ይህ ነው፤ በመካከላችሁ ያለ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። 11ስለዚህ ሁላችሁም ሸለፈታችሁን ትገረዛላችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ኪዳን ምልክት ይሆናል። 12የሚመጣውም ትውልድ ሁሉ፣ ማንኛውም ወንድ ልጅ፣ ስምንት ቀን ሲሞላው ይገረዝ፤ እንደዚሁም በቤትህ የተወለደውና ከውጭ በገንዘብ የተገዛ ባዕድ ሁሉ ይገረዝ። 13በቤትህ የተወለደም ሆነ በገንዘብህ የተገዛ ሁሉ መገረዝ አለበት፤ በሥጋችሁ የሚፈጸመው ይህ ኪዳኔ የዘላለም ኪዳን ይሆናል። 14የሥጋ ሸለፈቱን ያልተገረዘ ማንኛውም ወንድ ኪዳኔን በማፍረሱ ከወገኖቹ ይወገድ።”
15እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሦራን ከእንግዲህ ሦራ ብለህ አትጠራትም፤ ስሟ ከዛሬ ጀምሮ ሣራ ይሁን። 16እኔ እባርካታለሁ ከርሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ የብዙም ሕዝቦች እናት ትሆን ዘንድ እባርካታለሁ፤ የሕዝቦችም ነገሥታት ከርሷ ይወጣሉ።”
17አብርሃምም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ሣቀና በልቡ፣ “እንዲያው ምንስ ቢሆን የመቶ ዓመት ሽማግሌ የልጅ አባት መሆን ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመቷ ልጅ መውለድ ትችላለችን?” አለ። 18አብርሃም እግዚአብሔርን፣ “እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርህልኝ” አለው።
19እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ይሁን ዕሺ፤ ነገር ግን ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይሥሐቅ#17፥19 ይሥሐቅ ማለት ይሥቃል ማለት ነው። ብለህ ትጠራዋለህ፤ እኔም ከርሱ በኋላ ለዘሩ ሁሉ የሚሆን የዘላለም ኪዳን ከርሱ ጋራ እገባለሁ። 20ስለ እስማኤልም ቢሆን ልመናህን ሰምቼሃለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ፍሬያማም አደርገዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ የዐሥራ ሁለት አለቆች አባት ይሆናል፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ። 21ኪዳኔን ግን የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ልጅ፣ ከይሥሐቅ ጋራ አደርጋለሁ።” 22እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋራ መነጋገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ላይ ወጣ።
23በዚያችም ዕለት አብርሃም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ልጁን እስማኤልን፣ በቤቱ ውስጥ የተወለዱትንና ከውጭ በገንዘቡ የገዛቸውን ወንዶች በሙሉ ሸለፈታቸውን ገረዛቸው። 24አብርሃም ሸለፈቱን ሲገረዝ ዕድሜው 99 ዓመት ነበር። 25ልጁም እስማኤል ሸለፈቱን ሲገረዝ 13 ዓመቱ ነበር። 26አብርሃምና ልጁ እስማኤል፣ ሁለቱም በዚያ ቀን ተገረዙ። 27በአብርሃም ቤት ያሉ ወንዶች ሁሉ፣ በቤቱ የተወለዱትም ሆኑ ከውጭ በገንዘብ የተገዙ ከርሱ ጋራ ተገረዙ።

Currently Selected:

ዘፍጥረት 17: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in