YouVersion Logo
Search Icon

ሕዝቅኤል 37

37
የደረቅ ዐጥንቶች ሸለቆ
1 የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበረ፤ እርሱም በእግዚአብሔር መንፈስ አወጣኝ፤ በሸለቆ መካከልም አኖረኝ፤ ሸለቆውም በዐጥንቶች ተሞልቶ ነበር። 2በእነርሱም መካከል ወደ ፊትና ወደ ኋላ አመላለሰኝ፤ በሸለቆውም ወለል ላይ በጣም የደረቁ እጅግ ብዙ ዐጥንቶች አየሁ። 3እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ዐጥንቶች በሕይወት ሊኖሩ ይችላሉን?” ሲል ጠየቀኝ።
እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ብቻ ታውቃለህ” አልሁ።
4ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ለእነዚህ ዐጥንቶች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንት ደረቅ ዐጥንቶች፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ! 5ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ፤ ዐጥንቶች እንዲህ ይላል፤ እስትንፋስ#37፥5 በዕብራይስጥ ነፋስ ወይም መንፈስ ማለትም ነው (ከ6-14 ይመ)። አገባባችኋለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ። 6ጅማት አደርግላችኋለሁ፤ ሥጋ አለብሳችኋለሁ፤ በቈዳ እሸፍናችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ በሕይወት ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”
7ስለዚህ እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢቱን በምናገርበትም ጊዜ የኵሽኵሽታ ድምፅ ተሰማ፤ ዐጥንቶቹም አንድ ላይ ሆኑ፤ ዐጥንት ከዐጥንት ጋር ተጋጠመ። 8እኔም ተመለከትሁ፤ ጅማት ነበረባቸው፤ ሥጋም በላያቸው ታየ፤ ቈዳም ሸፍኗቸዋል፤ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም።
9ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለነፋሱ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ነፋስ ሆይ፤ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ በሕይወት እንዲኖሩም በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።’ ” 10ስለዚህም እንዳዘዘኝ ትንቢት ተናገርሁ፤ እስትንፋስም ገባባቸው፤ ሕያዋንም ሆኑ፤ እጅግ ታላቅ ሰራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
11ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ዐጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው፤ እንዲህም ይላሉ፤ ‘ዐጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋ የለንም፤ ተቈርጠናል።’ 12ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን እከፍታለሁ፤ ከውስጣቸው አወጣችኋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር መልሼ አመጣችኋለሁ። 13ከዚያም እናንተ ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን ከፍቼ ሳወጣችሁ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 14መንፈሴን በውስጣችሁ አስቀምጣለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፤ በገዛ ምድራችሁ አስቀምጣችኋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ፣ እንዳደረግሁትም ታውቃላችሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ”
አንድ ሕዝብ በአንድ ንጉሥ
15 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 16“የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ በትር ወስደህ፣ ‘የይሁዳና የተባባሪዎቹ የእስራኤላውያን’ ብለህ ጻፍበት። ከዚያም ሌላ በትር ወስደህ፣ ‘የኤፍሬም፣ የዮሴፍና የተባባሪዎቹ የእስራኤል ቤት ሁሉ’ ብለህ ጻፍበት። 17እንደ አንድ በትር ይሆኑ ዘንድ በእጅህ ላይ አጋጥመህ ያዛቸው።
18“የአገርህ ልጆች፣ ‘ይህስ ምን ማለትህ እንደ ሆነ አትነግረንምን?’ ብለው ሲጠይቁህ፣ 19እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን በትርና የተባባሪዎቹን የእስራኤላውያንን ነገድ በትር እወስዳለሁ፤ ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥሜ አንድ ወጥ በትር አደርጋቸዋለሁ፤ እነርሱም በእጄ አንድ በትር ይሆናሉ።’ 20የጻፍህባቸውን በትሮች ከፊት ለፊታቸው ያዝ፤ 21እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እስራኤላውያንን ከሄዱባቸው አሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየስፍራው ሰብስቤ ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ። 22በምድሪቱ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፤ በሁሉም ላይ አንድ ንጉሥ ይነግሣል፤ ከእንግዲህም ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፤ መንግሥታቸውም ከሁለት አይከፈልም። 23በጣዖቶቻቸው፣ በአጸያፊ ምስሎቻቸው ወይም በማንኛውም ኀጢአት ራሳቸውን አያረክሱም፤ ነገር ግን እኔን በመተው ከሠሩት ኀጢአት ሁሉ አድናቸዋለሁ፤#37፥23 በብዙ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆችም እንዲሁ (በተጨማሪ ሰብዓ ሊቃናት ይመ) ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆች ግን ኀጢአት የሠሩባቸውን የመኖሪያ ስፍራዎቻቸውን ሁሉ ይላሉ። አነጻቸዋለሁም። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።
24“ ‘ባሪያዬ ዳዊት በላያቸው ይነግሣል፤ ሁሉም አንድ እረኛ ይኖራቸዋል፤ ሕጌን ይከተላሉ፤ ሥርዐቴንም በጥንቃቄ ይጠብቃሉ። 25አባቶቻችሁ በኖሩበት፣ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠሁት ምድር ይኖራሉ። በዚያም እነርሱ፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘላለም ይኖራሉ፤ ባሪያዬ ዳዊትም ለዘላለም ንጉሣቸው ይሆናል። 26ከእነርሱም ጋር የሰላም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ቃል ኪዳኑም የዘላለም ይሆናል። አጸናቸዋለሁ፤ አበዛቸዋለሁ፤ መቅደሴንም በመካከላቸው ለዘላለም አኖራለሁ። 27ማደሪያዬ ከእነርሱ ጋር ይሆናል፤ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። 28መቅደሴም ለዘላለም በመካከላቸው በሚሆንበት ጊዜ፣ አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ቀደስሁ ያውቃሉ።’ ”

Currently Selected:

ሕዝቅኤል 37: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in