YouVersion Logo
Search Icon

ሕዝቅኤል 13

13
የሐሰተኛ ነቢያት መወገዝ
1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት በሚናገሩት በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፤ ከገዛ ራሳቸው ትንቢት የሚናገሩትን እንዲህ በላቸው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ 3ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አንዳች ነገር ሳያዩ የራሳቸውን መንፈስ ለሚከተሉ ሞኞች#13፥3 ወይም ክፉዎች ነቢያት ወዮላቸው! 4እስራኤል ሆይ፤ ነቢያትሽ በፍርስራሽ መካከል እንደሚኖሩ ቀበሮዎች ናቸው። 5በእግዚአብሔር ቀን በሚሆነው ጦርነት ጸንቶ መቆም እንዲችል፣ የተሰነጠቀውን ቅጥር ለእስራኤል ቤት ለመጠገን ወደዚያ አልወጣችሁም። 6ራእያቸው ሐሰት፣ ትንቢታቸው ውሸት ነው፤ እግዚአብሔር ሳይልካቸው፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ይላሉ፤ ይህም ሆኖ የተናገሩት ይፈጸማል ብለው ይጠብቃሉ። 7እኔ ሳልናገር፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ስትሉ ሐሰተኛ ራእይ ማየታችሁ፣ ውሸተኛስ ትንቢት መናገራችሁ አይደለምን?
8“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቃላችሁ ሐሰት፣ ራእያችሁም ውሸት ስለሆነ እኔ በእናንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር9እጄ የሐሰት ራእይ በሚያዩና በሚያሟርቱ ነቢያት ላይ ተነሥቷል። የሕዝቤ ጉባኤ ተካፋይ አይሆኑም፤ በእስራኤል ቤት መዝገብ አይጻፉም፤ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም። በዚያ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።”
10“ ‘ሰላም ሳይኖር፣ “ሰላም አለ” እያሉ ሕዝቤን ያስታሉ፤ ሕዝቡ ካብ ሲሠራ እነርሱ በኖራ ይለስናሉ፤ 11ስለዚህ በኖራ ለሚለስኑት ካቡ እንደሚወድቅ ንገራቸው። ዶፍ ይወርዳል፤ ታላቅ የበረዶ ድንጋይ እሰድዳለሁ፤ ዐውሎ ነፋስም ይነሣል። 12እነሆ ካቡ ሲፈርስ ሕዝቡ “የለሰናችሁበት ኖራው ወዴት ሄደ?” ብለው አይጠይቋችሁምን?
13“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመዓቴ ዐውሎ ነፋስ እሰድዳለሁ፣ በቍጣዬ የበረዶ ድንጋይ እልካለሁ፤ ዶፍም ከታላቅ ጥፋት ጋር ይወርዳል። 14በኖራ የለሰናችሁትን ካብ አፈርሳለሁ፤ መሠረቱም ተገልጦ እስኪታይ ድረስ ከምድር ጋር አደባልቀዋለሁ። ቅጥሩ#13፥14 ወይም ከተማው በሚወድቅበት ጊዜ፣ እናንተም በውስጡ ታልቃላችሁ። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 15መዓቴንም በቅጥሩና ኖራ በለሰኑት ሰዎች ላይ እሰድዳለሁ፤ እናንተንም እንዲህ እላችኋለሁ፤ “ቅጥሩና ቅጥሩን በኖራ የለሰኑት የሉም፤ 16ኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገሩላትና ሰላም ሳይኖር የሰላም ራእይ ያዩላት የእስራኤል ነቢያት ጠፍተዋል”፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’
17“አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፤ ከራሳቸው አመንጭተው ትንቢት ወደሚናገሩ ወደ ሕዝብህ ሴቶች ልጆች ፊትህን መልስ፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፤ 18እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሕዝብን ነፍስ ለማጥመድ፣ ለአስማታቸው ለእጃቸው አንጓ ሁሉ አሸንክታብ ለሚያሰፉና፣ የተለያየ መጠን ያለውን የራስ መሸፈኛ ለሚያበጁ ሴቶች ወዮላቸው! በውኑ የሕዝቤን ነፍስ እያጠመዳችሁ የራሳችሁን ነፍስ ታድናላችሁን? 19ዕፍኝ ለማይሞላ ገብስና ለቍራሽ እንጀራ ስትሉ ሐሰትን የሚያደምጥ ሕዝቤን እየዋሻችሁ መሞት የማይገባውን በመግደል፣ መኖር የማይገባውንም በማትረፍ በሕዝቤ መካከል አርክሳችሁኛል።”
20“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ የሕዝብን ነፍስ እንደ ወፍ በምታጠምዱበት አሸንክታብ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ከክንዳችሁ ላይ እቀዳድደዋለሁ፤ እንደ ወፍ የምታጠምዱትንም ሕዝብ ነጻ አወጣዋለሁ። 21መሸፈኛችሁን ቀድጄ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ በቍጥጥራችሁ ሥር አይሆኑም፤ በዚያ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 22እኔ ያላሳዘንሁትን ጻድቅ በውሸት ስላሳዘናችሁ፣ ኀጢአተኛም ከክፉ መንገዱ ተመልሶ ሕይወቱን እንዳያድን በኀጢአቱ ስላበረታታችሁት፣ 23ከእንግዲህ የሐሰት ራእይ አታዩም፣ ሟርትም አታሟርቱም፤ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።” ’ ”

Currently Selected:

ሕዝቅኤል 13: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in