YouVersion Logo
Search Icon

ዘፀአት 9

9
የእንስሳት ዕልቂት
1ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ፈርዖን ሂድና እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ (ኤሎሂም) እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ “ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።” 2አሁንም እንዳይሄዱ ብታደርግና ብትከለክላቸው፣ 3የእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅ በመስክ ላይ ባሉት እንስሳት፣ በፈረሶችህና በአህዮችህ፣ በግመሎችህና በቀንድ ከብቶችህ፣ በበጎችህና በፍየሎችህ ላይ አስከፊ መቅሠፍት ያመጣብሃል። 4ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤልና በግብፅ እንስሳት መካከል ልዩነት ያደርጋል፤ ይኸውም የእስራኤል የሆነ ማንኛውም እንስሳ እንዳይሞት ነው።’ ”
5 እግዚአብሔር (ያህዌ) ጊዜን ወስኖ፣ እንዲህ አለ፤ “በነገው ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) በምድሪቱ ላይ ይህን ያደርጋል።” 6በማግሥቱም እግዚአብሔር (ያህዌ) ነገሩን ፈጸመው፤ የግብፃውያን እንስሳት በሙሉ ዐለቁ፤ ነገር ግን የእስራኤላውያን ከሆኑት እንስሳት አንድም አልሞተም። 7ፈርዖን ያጣሩ ዘንድ ሰዎች ልኮ ከእስራኤላውያኑ እንስሳት አንድም እንኳ አለመሞቱን ተገነዘበ። ያም ሆኖ ልቡ እንደ ደነደነ ስለ ነበር፣ ሕዝቡን አልለቀቀም።
የዕባጭ መቅሠፍት
8ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን አላቸው፤ “ከምድጃው ዕፍኝ ዐመድ ወስዳችሁ፣ ሙሴ በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው። 9በግብፅ ምድር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፤ በምድሪቱ ሁሉ በሚገኙት ሰዎችና እንስሳት ላይ መግል የያዘ ዕባጭ ይወጣል።”
10ስለዚህ ከምድጃው ዐመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፤ መግል የያዘ ዕባጭም በሰዎችና በእንስሳት ላይ ወጣ። 11በእነርሱና በግብፃውያን ሁሉ ላይ ዕባጭ ወጥቶ ስለ ነበር፣ አስማተኞቹ በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም። 12እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ እንደ ተናገረውም፣ ሙሴንና አሮንን መስማት አልፈለገም።
የበረዶ መቅሠፍት
13ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ማልደህ በጧት ተነሣ፤ ከፈርዖን ፊት ቀርበህ እንዲህ በለው፤ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) የሚለው ይህ ነው፤ ‘ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤ 14አለዚያ በአንተ በሹማምትህና በሕዝብህ ላይ የመቅሠፍቴን መዓት ሁሉ አሁን አወርድብሃለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ ነው። 15አሁን እጄን ዘርግቼ አንተንና ሕዝብህን ከገጸ ምድር ሊያጠፋችሁ በሚችል መቅሠፍት በመታኋችሁ ነበር። 16ነገር ግን ኀይሌን እንዳሳይህና ስሜም በምድር ዙሪያ ሁሉ እንዲታወቅ ለዚህ አስነሥቼሃለሁ።#9፥16 ወይም፣ ለዚህ ምሕረቴን አሳይቼሃለሁ 17እስካሁንም በሕዝቤ ላይ እንደ ተነሣህ ነው፤ ይሄዱም ዘንድ አትለቅቃቸውም። 18ስለዚህ ነገ በዚህ ጊዜ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በግብፅ ላይ ወርዶ የማያውቅ አስከፊ የበረዶ ማዕበል እልካለሁ። 19ከብቶችህና በመስክ ላይ ያለህ ማንኛውም ነገር ወደ መጠለያ ይገቡ ዘንድ አሁን ትእዛዝ ስጥ፤ ምክንያቱም በረዶው ወደ መጠለያ ባልገቡትና በመስክ ላይ በቀሩት በማንኛውም ሰውና እንስሳት ላይ ወርዶባቸው ስለሚሞቱ ነው።’ ”
20 የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃል የፈሩት የፈርዖን ሹማምት፣ ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን ለማስገባት ተጣደፉ። 21የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃል ችላ ያሉት ግን ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን በመስክ ላይ እንደ ነበሩ ተዉአቸው።
22ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “በመላዪቱ የግብፅ ምድር ባሉት ሰዎች፣ በእንስሳት እንዲሁም በምድሪቱ ላይ በሚበቅሉት ነገሮች ሁሉ ላይ በረዶ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ አንሣ” አለው። 23ሙሴ በትሩን ወደ ሰማይ ባነሣ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነጐድጓድና በረዶ አወረደ፤ መብረቅም በምድሪቱ ላይ ሆነ። እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፅ ምድር በረዶ አዘነበ፤ 24በረዶ ወረደ፤ መብረቅም አብረቀረቀ፤ ግብፅ አገር ከሆነችበት ዘመን አንሥቶ በምድሪቱ ሁሉ እንደዚህ ያለ አስከፊ ማዕበል ሆኖ አያውቅም። 25በመላው ግብፅ በረዶ በመስክ ላይ ያለውን ሁሉ፣ ሰዎችንና እንስሳትንም መታ፤ በመስክ ላይ የበቀለውን ሁሉ አጠፋ፤ ዛፉን ሁሉ ባዶ አስቀረ። 26በረዶ ያልወረደበት ቢኖር እስራኤላውያን የሚኖሩበት የጌሤም ምድር ብቻ ነበር።
27ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠራ፤ እንዲህም አላቸው፤ “አሁንስ በድያለሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ትክክል ነው፤ እኔና ሕዝቤ ግን ስተናል። 28መብረቅና በረዶ በዝቶብናልና ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸልዩልን፤ እንድትሄዱ እለቃችኋለሁ፤ ከዚህ በኋላ በዚህ የመኖር ግዴታ የለባችሁም።”
29ሙሴም መልሶ፣ “ከከተማዋ በወጣሁ ጊዜ፣ እጆቼን ለጸሎት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) እዘረጋለሁ፤ አንተም ምድር የእግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ሆነች ታውቅ ዘንድ መብረቁ ያቆማል፤ ከእንግዲህ በኋላ በረዶ አይኖርም። 30ሆኖም አንተና ሹማምትህ አሁንም ቢሆን እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላክን እንደማትፈሩ ዐውቃለሁ።”
31ተልባው አብቦ፣ ገብሱም ፍሬ ይዞ ስለ ነበር፣ ተልባውና ገብሱ ከጥቅም ውጭ ሆኑ። 32ስንዴውና አጃው ግን በዚያ ወቅት ባለማፍራቱ አልጠፋም ነበር።
33ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ከከተማው ወጣ። እጁን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዘረጋ፤ ነጐድጓዱና በረዶው ቆመ፤ ዝናቡም በምድሪቱ ላይ መዝነቡን አቆመ። 34ፈርዖንም ዝናቡ፣ በረዶውና ነጐድጓዱ መቆሙን ባየ ጊዜ እንደ ገና በደለ፤ እርሱና ሹማምቱ ልባቸውን አደነደኑ። 35ስለዚህ የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ እንደ ተናገረውም እስራኤላውያን ይሄዱ ዘንድ አልለቀቃቸውም።

Currently Selected:

ዘፀአት 9: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in