ዘፀአት 26
26
የማደሪያው ድንኳን
26፥1-37 ተጓ ምብ – ዘፀ 36፥8-38
1“በቀጭኑ ከተፈተለ የበፍታ ድርና በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ በተሠሩ ዐሥር መጋረጃዎች ማደሪያ ድንኳኑን ሥራ፤ እጀ ብልኅ ሠራተኛም ኪሩቤልን ይጥለፍባቸው። 2መጋረጃዎች ሁሉ እኵል ይሁኑ፤ የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሃያ ስምንት ክንድ ወርዱም አራት ክንድ#26፥2 ርዝመቱ 12.5 ሜትር ወርዱ 1.8 ሜትር ያህል ነው። ይሁን። 3አምስቱን መጋረጃዎች አገጣጥመህ ስፋ፤ የቀሩትንም አምስት መጋረጃዎች እንደዚሁ አገጣጥመህ ስፋቸው። 4ከዳር በኩል ባለው መጋረጃ ጠርዝ ላይ፣ ከሰማያዊ ጨርቅ የተሠሩ ቀለበቶች አድርግ፤ በሌላውም የመጋረጃ ጠርዝ ላይ እንዲሁ አድርግ። 5ቀለበቶችን ትይዩ በማድረግ አምሳ ቀለበቶችን በአንደኛው ጠርዝ መጋረጃ፣ አምሳ ቀለበቶችንም በሌላው ጠርዝ መጋረጃ አድርግ። 6ከዚያም የመገናኛው ድንኳን አንድ ወጥ ይሆን ዘንድ መጋረጃዎቹን በአንድ ላይ ለማያያዝ አምሳ የወርቅ ማያያዣዎችን ሥራ።
7“ማደሪያ ድንኳኑን ከላይ ሆነው የሚሸፍኑ ዐሥራ አንድ የፍየል ጠጕር መጋረጃዎች ሥራ። 8ዐሥራ አንዱም መጋረጃዎች እኩል ይሁኑ፤ የእያንዳንዱ ርዝመት ሠላሳ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ#26፥8 ርዝመቱ 13.5 ሜትር ወርዱ 1.8 ሜትር ያህል ነው። ይሁን። 9አምስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ፣ እንደዚሁም ስድስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ አድርገህ ስፋቸው፤ ከማደሪያው ድንኳን ፊት ለፊት ስድስተኛውን መጋረጃ ዕጠፍና በላዩ ላይ ደርበው። 10በአንድ በኩል ባለው መጨረሻ መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶችን፣ እንዲሁም በሌላ በኩል ባለው መጨረሻ መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶችን አድርግ። 11ከዚያም አምሳ የናስ ማያያዣዎችን ሥራ፤ ድንኳኑን አንድ ወጥ አድርጎ ለማያያዝ በቀለበቶቹ ውስጥ ጨምራቸው። 12ስለ ድንኳኑ መጋረጃዎች ትርፍ ቁመትም፣ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ ከማደሪያው ድንኳን ጀርባ ላይ እንዲንጠለጠል ይሁን። 13የድንኳኑ መጋረጃዎች በሁለቱም ጐኖች አንድ ክንድ ርዝመት#26፥13 ርዝመቱ 0.5 ሜትር ያህል ነው። ይኖራቸዋል፤ የተረፈውም የማደሪያውን ድንኳን ጐኖች እንዲሸፍን ሆኖ ይንጠለጠላል፤ 14ለድንኳኑ በቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቈዳ ልብስ አብጅ፤ በላዩም ላይ የአቆስጣ ቈዳ ይሁን#26፥14 ይህ የባሕር አውሬ ነው።።
15“ለማደሪያው ድንኳን ከግራር ዕንጨት ወጋግራዎችን አብጅ። 16እያንዳንዱም ወጋግራ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል#26፥16 ርዝመቱ 4.5 ሜትር፣ ወርዱ 0.7 ሜትር ያህል ነው። ይሁን፤ 17ሁለት ጕጦችም ጐን ለጐን ይሁኑለት፤ የማደሪያውን ድንኳን ወጋግራዎች ሁሉ በዚሁ መልክ አብጅ። 18ለማደሪያው ድንኳን ክፍል ሃያ ወጋግራዎችን ሥራ። 19ከሥራቸው የሚሆኑ አርባ የብር መቆሚያዎችን አብጅ፤ በእያንዳንዱ ጕጠት ሥር አንድ መቆሚያ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱም ወጋግራ ሁለት መቆሚያዎች ይኑሩ። 20በሌላው ጐን፣ ከማደሪያው ድንኳን በስተ ሰሜን በኩል ሃያ ወጋግራዎችን አብጅ፤ 21በእያንዳንዱም ወጋግራ ሥር ሁለት ሁለት መቆሚያ ሆኖ አርባ የብር መቆሚያዎችን አብጅ። 22በዳር በኩል ለሚገኘው ይኸውም በምዕራብ ጠርዝ ላለው የማደሪያው ድንኳን ስድስት ወጋግራዎች አብጅ። 23ዳርና ዳር ላሉት ማእዘኖች ሁለት ወጋግራዎች አብጅ። 24በእነዚህ ሁለት ማእዘኖች ላይ ከታች እስከ ላይ ድረስ ድርብ ሲሆኑ፣ በአንድ ቀለበት ውስጥ የሚገጥሙ መሆን አለባቸው፤ በሁለቱም ወገን እንዲሁ መሆን አለበት። 25ስለዚህ ስምንት ወጋግራዎች አሉ፤ እንዲሁም ዐሥራ ስድስት የብር መቆሚያዎች ሲኖሩ፣ ለእያንዳንዱ ወጋግራ ሁለት ሁለት መቆሚያ ይሆናል።
26“ደግሞም ከግራር ዕንጨት አግዳሚዎችን አብጅ፤ በአንድ በኩል ላሉት የማደሪያው ድንኳን ወጋግራዎች አምስት፣ 27በሌላው ጐን ላሉት አምስት፣ በማደሪያው ድንኳን ዳር በምዕራብ በኩል ባሉት ወጋግራዎች አምስት አብጅ። 28መካከለኛው አግዳሚ በወጋግራዎቹ መካከል ከጫፍ እስከ ጫፍ ይተላለፍ። 29ወጋግራዎቹን በወርቅ ለብጣቸው፤ አግዳሚዎቹን ለመያዝ የወርቅ ቀለበቶች አብጅ፤ አግዳሚዎቹንም በወርቅ ለብጣቸው።
30“ማደሪያ ድንኳኑንም በተራራው ላይ ባየኸው ዕቅድ መሠረት ትከለው።
31“ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ አብጅ፤ እጀ ብልኅ ሠራተኛም ኪሩቤልን ይጥለፍበት። 32በወርቅ በተለበጡ ከግራር ዕንጨት በተሠሩና በአራቱ የብር መቆሚያዎች ላይ በቆሙት በአራቱ ምሰሶዎች፣ በወርቅ ኵላቦች ላይ አንጠልጥለው። 33መጋረጃውን በማያያዣዎቹ ላይ ስቀለው፤ የምስክሩንም ታቦት ከመጋረጃው በስተ ኋላ አስቀምጠው፤ መጋረጃውም መቅደሱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ ይለያል። 34በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ በምስክሩ ታቦት ላይ የማስተስረያውን ክዳን አስቀምጥ። 35ጠረጴዛውን ከመገናኛው ድንኳን በሰሜን በኩል ከመጋረጃው ውስጥ አስቀምጠው፤ መቅረዙንም ከእርሱ ትይዩ በማድረግ በደቡብ በኩል አድርገው።
36“ለድንኳኑ ደጃፍ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ በጥልፍ ዐዋቂ የተጠለፈ መጋረጃ አብጅ። 37ለዚህም መጋረጃ የወርቅ ኵላቦችንና ከግራር ዕንጨት የተሠሩ፣ በወርቅ የተለበጡ አምስት ምሰሶዎችን አብጅ፤ አምስት የናስ መቆሚያዎችንም አብጅላቸው።
Currently Selected:
ዘፀአት 26: NASV
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.