መክብብ 6
6
1ከፀሓይ በታች ሌላ ክፉ ነገር አየሁ፤ እርሱም ለሰዎች እጅግ የሚከብድ ነው፤ 2ሰው ልቡ የሚሻውን እንዳያጣ፣ አምላክ ባለጠግነትን፣ ሀብትንና ክብርን ይሰጠዋል፤ አምላክ ግን እንዲደሰትበት ሥልጣን አልሰጠውም፤ ይልቁን ባዕድ ይደሰትበታል። ይህም ከንቱ፣ እጅግም ክፉ ነገር ነው።
3አንድ ሰው መቶ ልጅ ሊኖረውና ብዙ ዓመት ሊኖር ይችላል፤ ምንም ያህል ይኑር፣ በሀብቱ ደስ ካልተሠኘበትና በአግባብ ካልተቀበረ፣ ከርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል እላለሁ፤ 4ምክንያቱም በከንቱ ይመጣል፤ በጨለማም ይሄዳል፤ ስሙም በጨለማ ተሸፍኗል። 5ፀሓይን ባያይና ምንም ነገር ባያውቅ እንኳ፣ እርሱ ከዚያ ሰው ይልቅ ዕረፍት አለው፤ 6ሁለት ጊዜ ሺሕ ዓመት ቢኖር፣ ነገር ግን በሀብቱ ደስ ባይሠኝበት፣ ሁሉ ወደዚያ ስፍራ የሚሄድ አይደለምን?
7የሰው ጥረት ሁሉ ለአፉ ነው፤
ፍላጎቱ ግን ፈጽሞ አይረካም።
8ጠቢብ ከሞኝ ይልቅ ምን ብልጫ አለው?
ድኻስ በሌሎች ፊት እንዴት እንደሚኖር በማወቁ፣
ትርፉ ምንድን ነው?
9በምኞት ከመቅበዝበዝ፣
በዐይን ማየት ይሻላል፤
ይህም ደግሞ ከንቱ፣
ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
10አሁን ያለው ሁሉ አስቀድሞ ስም የተሰጠው ነው፤
ሰው የሚሆነውም አስቀድሞ የታወቀ ነው፤
ከራሱ ይልቅ ከሚበረታ ጋራ፣
ማንም አይታገልም።
11ቃል በበዛ ቍጥር፤
ከንቱነት ይበዛል፤
ይህ ታዲያ ለሰው ምን ይጠቅማል?
12ሰው በሕይወት ሳለ፣ እንደ ጥላ በሚያልፉት ጥቂትና ከንቱ በሆኑት ቀኖቹ፣ ለሰው መልካም የሆነውን የሚያውቅ ማን ነው? እርሱ ከሄደ በኋላስ ከፀሓይ በታች የሚሆነውን ማን ሊነግረው ይችላል?
Currently Selected:
መክብብ 6: NASV
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.