YouVersion Logo
Search Icon

ዘዳግም 25

25
1በሰዎች መካከል ጠብ ቢነሣና ወደ ፍርድ አደባባይ ቢሄዱ፣ ዳኞች ተበዳይን ነጻ፣ በዳይን ግን ጥፋተኛ በማድረግ የፍርድ ውሳኔ ይስጡ። 2በደለኛው ሰው መገረፍ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ዳኛው መሬት ላይ ያጋድመው፤ ለጥፋቱ ተመጣጣኝ የሆነ ግርፋት እርሱ ባለበት ይገረፍ። 3ሆኖም ግርፋቱ ከአርባ የሚበልጥ አይሁን፤ ከዚህ ካለፈ ግን፣ ወንድምህ በፊትህ የተዋረደ ይሆናል።
4የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር።
5ወንድማማቾች በአንድነት ቢኖሩና ከእነርሱ አንዱ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ የሟቹ ሚስት ከቤተ ሰቡ ውጭ ባል ማግባት የለባትም። የባሏ ወንድም ይውሰዳትና ያግባት፤ የዋርሳነት ግዴታውንም ይፈጽምላት። 6በመጀመሪያ የምትወልደውም ልጅ ስሙ ከእስራኤል ፈጽሞ እንዳይጠፋ በሟች ወንድሙ ስም ይጠራ።
7ሆኖም ግን አንድ ሰው የወንድሙን ሚስት ለማግባት ባይፈልግ፣ ሴትዮዋ በከተማዪቱ በር ወዳሉት ሽማግሌዎች ሄዳ፣ “የባለቤቴ ወንድም የወንድሙን ስም በእስራኤል ለማስጠራት አልፈለገም፤ የዋርሳነት ግዴታውንም አልፈጸመልኝም” ትበላቸው። 8ከዚያም የከተማው ሽማግሌዎች ያን ሰው ጠርተው ያነጋግሩት፤ እርሱም፣ “እርሷን ላገባት አልፈልግም” ብሎ በሐሳቡ ቢጸና፣ 9የወንድሙም ሚስት በሽማግሌዎች ፊት ወደ እርሱ ቀርባ፣ የአንድ እግሩን ጫማ በማውለቅ በፊቱ ላይ ትትፋበትና “የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ እንዲህ ያለው ድርጊት ይፈጸምበታል” ትበል። 10የዚያም ሰው የዘር ሐረግ በእስራኤል ዘንድ፣ “ጫማው የወለቀበት ቤት” ተብሎ ይታወቃል።
11ሁለት ሰዎች ቢደባደቡ፣ የአንደኛው ሚስት ባሏን ከደብዳቢው እጅ ለማስጣል መጥታ፣ እጇን ዘርግታ ብልቱን ብትይዘው፣ 12እጇን ቍረጠው፤ አትራራላት።
13በከረጢትህ ውስጥ ከባድና ቀላል የሆኑ ሁለት የተለያዩ ሚዛኖች አይኑሩህ። 14በቤትህም ውስጥ ትልቅና ትንሽ የሆኑ ሁለት የተለያዩ መስፈሪያዎች አይኑሩህ። 15አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፣ ጻድቅና የታመነ ሚዛንና መስፈሪያ ይኑርህ። 16አምላክህ እግዚአብሔር እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽመውንና የሚያምታታውን ሁሉ ይጸየፈዋልና።
17ከግብጽ በወጣህ ጊዜ፣ አማሌቅ በመንገድ በአንተ ላይ ያደረገብህን አስታውስ፤ 18ደክመህና ዝለህ በነበርህበት ጊዜ፣ በጕዞ ላይ አግኝተውህ፣ ከኋላ ያዘግሙ የነበሩትን ሁሉ ገደሉ፤ እግዚአብሔርንም አልፈሩም። 19አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ዙሪያ ካሉት ጠላቶችህ ሁሉ ባሳረፈህ ጊዜ፣ ከሰማይ በታች ያለውን የአማሌቅን መታሰቢያ ደምስስ፤ ከቶ እንዳትረሳ!

Currently Selected:

ዘዳግም 25: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in